“የሕዝባችን ቀዳሚ ምርጫው ሰላም፤ ፍላጎቱም ልማት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

54

ባሕር ዳር: ሚያዚያ: 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉ ሕዝብ ተቀዳሚ ምርጫ ሰላም መኾኑን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት አስታውቀዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ በመልዕክታቸው በክልላችን በተለያዩ አካባቢዎች በግንባታ ሂደት ላይ የነበሩ የትምህርት እና የጤና ተቋማት ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል። የአማራ ሕዝብ ቀዳሚ ምርጫው ሰላም፤ ፍላጎቱም ልማት ነው ብለዋል። የዛሬም ኾነ የወደፊት አቋሙ ሰላም እና ልማት፤ እድገትና ብልጽግና እንደኾነ አረጋግጧል ነው ያሉት።

ከእርስ በርስ ግጭት ጥፋት እንጂ የሚገኝ የግልም ኾነ የጋራ ጥቅም እና ስኬት እንደማይኖር በተከታታይ በተፈጠሩ የጋራ መድረኮች ደጋግሞ አንስቷል። የልማትም ይሁን የተጠቃሚነት አጀንዳዎቹ በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱለት አጥብቆ ጠይቋል። ለሰላም ያለውን አቋም በአደባባይ ገልጿል።

ሰላም የምርጫ ጉዳይ አይደለም። የሁሉም አካል የሕልውና ጉዳይ ነው። ሰላም በራቀን ጊዜ የምናጣው እንጅ የምናተርፈው እንደሌለ ከእኛ በለይ አስረጂ እና ምስክር ሊኖር አይችልም። ሰላም እና ልማትም አይነጣጠሉም። የመልማት እና የመለወጥ ፍላጎታችን የሚረጋገጠው ሰላማችን በጋራ ጥረት ማጽናት ስንችል ነው ብለዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በክልላችን የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ክልላችን መልማት በሚችለው ሃብቱ ልክ እንዳይለማ፤ ሕዝባችን ባለው የሥራ ዘርፍ እንዲሁም በአቅም እና ፍላጎቱ መጠን በነጻነት ተንቀሳቅሶ ሰርቶ ራሱን እና አካባቢውን እንዳይለውጥ ገርጋሪ ምክንያት ኾኖ ቆይቷል ነው ያሉት።

ሰላምን ለማጽናት በሠራነው ቅንጅታዊ ሥራ አማራ ክልል ወደ ቀደመ ሰላሙ እየተመለሰ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በሌላ በኩል ልማት ላይ ትኩረት አድርገን ባደረግነው እርብርብ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይም ለክልላችን ሰላም እና ልማት መረጋገጥ የምናደርገወን ያላሰለሰ ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“17 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክት በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
Next articleከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በጎንደር ከተማ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን ምገባ መርሐ ግብር እየጎበኙ ነው።