“17 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክት በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

20

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እየተገነቡ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በከተማዋ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። 22 ኪሎሜትር የመንገድ ፕሮጀክት እየተገነባ መኾኑን ነው የተናገሩት። በከተማ አሥተዳደሩ በጀት የሚገነባው መንገዱ ከ20 እስከ 40 ሜትር ስፋት እንዳላውም ገልጸዋል።

መንገዱ የአስፋልት ኮንክሪት መኾኑንም ተናግረዋል። በዚህ ዓመት 17 ኪሎ ሜትር መንገድ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚኾንም ገልጸዋል። አምስት ኪሎ ሜትር ብቻ ወደ ሚቀጥለው ዓመት ሊሸጋገር ይችላል ነው ያሉት። ሁሉም መንገዶች የግሪን ኤሪያ፣ የብስክሌት መንገድ፣ የእግረኛ መንገድ ያላቸው እና ደረጃቸውን የጠበቁ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

የመንገድ ዳር እና የጣና ሐይቅ ዳር ሥራዎችን ያካተተ የኮሪደር ልማት እየሠራን ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የኮሪደር ልማት ሥራው የከተማዋን ውበት እየገለጠ ነው ብለዋል። እስካሁን ሲሠሩ ከቆዩት የኮሪደር ልማት ሥራዎች በተጨማሪ ሌሎች ሥራዎችም እንደሚሠሩ ነው ያመላከቱት።

የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ በመጠናቀቅ ላይ መኾኑንም አስታውቀዋል። ሁለተኛውን ምዕራፍም በፍጥነት ለመጨረስ ርብርብ እየተደረገ መኾኑን ነው የገለጹት። ከመንገድ እና ከኮሪደር ልማት ሥራዎች ባለፈ የከተማ አሥተዳደሩን የመሬት አሥተዳደር እያዘመኑ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
የከተማውን መሬት በዘመናዊ መንገድ በመመዝገብ ለማሥተዳደር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የተቋም ግንባታዎችን የሚያጠናክሩ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችም እየተሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። የስማርት ሲቲ ሥራዎችም በትኩረት እየተሠሩ ነው ብለዋል። የከተማዋን እድገት ወደፊት የሚያስፈነጥሩ ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። የነዋሪዎችን መታወቂያ ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

የከተማዋ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተረጋጋ፣ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውም እየጨመረ መኾኑን ተናግረዋል። ባሕር ዳር ከተማ አሁን ላይ የሚኖርባት፣ የሚሠራባት፣ የሚጎበኟት እና የሚዝናኑባት ከተማ ናት ብለዋል። እየተሠራ ያለው የልማት ሥራ የከተማዋን የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንደሚያሳድገውም ገልጸዋል። በከተማዋ 129 ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት እየተላለፈ መኾኑንም ተናግረዋል።

ለኢንቨስትመንት የሚመጡ ባለሃብቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ዋነኛ ዓላማ የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ከፍ እንዲያደርጉ ነው ብለዋል።

በከተማዋ እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ እንደሚኾንም ገልጸዋል። የልማት ሥራዎቹ የባሕር ዳርን የቀደመ ውበት የበለጠ እየገለጡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች እንዲመጡ የሚያስችል ነው ብለዋል። አሁን ላይም የከተማዋ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እየጨመረ መምጣቱን ነው የተናገሩት።

ባሕር ዳር እየለማች ያለች የመዝናኛ ከተማ ናት ብለዋል። የኢንቨስትመንት ጥያቄውም እየጨመረ መምጣቱን ነው የተናገሩት። ከተማ አሥተዳደሩ የልማት ዕቅዳቸውን እያየ ለባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ቦታ እንደሚሰጥም ገልጸዋል። ባሕር ዳርን የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ እንደሚሠራም አመላክተዋል።

ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው እንዲያለሙ፣ ጎብኝዎችም ወደ ከተማዋ መጥተው እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበደቡብ ጎንደር ዞን ከተለያዩ ወረዳዎች መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል የተመለመሉ ወጣቶች ሽኝት ተደረገላቸው።
Next article“የሕዝባችን ቀዳሚ ምርጫው ሰላም፤ ፍላጎቱም ልማት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ