
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከቀበሌ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የአንድ ወር ደመወዛቸውን በከተማዋ ለሚገነባው የኮሪደር ልማት እንዲውል ሰጥተዋል። የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ እና ሌሎችም የክልሉ መሪዎች በየደረጃው ከሚገኙ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አመራሮች ጋር በከተማው ስለሚከናወነው ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ እና የሃብት አሰባሰብ ዙሪያ ተወያይተዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ “ጎንደር በመላ ኢትዮጵያውያን የምትገነባ፣ መላ ኢትዮጵያውያንም በጋራ ሠርተው በፍቅር የሚኖሩባት ከተማ ናት” ብለዋል። ኢትዮጵያውያን ለጎንደር ከተማ ኮሪደር ልማት ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ አዋጥተዋል፤ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች እና መሪዎችም በሚችሉት መንገድ ሁሉ ተባብረው ከተማዋን ማልማት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ከአምስት ዓመት ሕጻን ጨምሮ መላ ኢትዮጵያውያን የሚችሉትን ሁሉ ለጎንደር ሰጥተዋል ብለዋል። ይህ ጎንደር በመላ ኢትዮጵያውያን መወደድ ብቻ ሳይኾን በጋራ የሚገነቧት ከተማ መኾኗንም አሳይቶናል ብለዋል።
የከተማው አመራሮችም ሕዝቡን እየመሩ ለሰላም እና ለልማት ከማሰለፍ በተጨማሪ የአንድ ወር ደመወዝ መስጠታቸውን ከንቲባው ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ አመራሮችም የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለከተማቸው ልማት በደስታ እንደሚሰጡ ተናግረዋል። እንደየደረጃቸው የሚመሩት ሕዝብ ለጎንደር ከተማ ልማት በሚችለው ሁሉ ተባብሮ አሻራውን እንዲያስቀምጥም በትጋት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን