
ደሴ: ሚያዝያ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “በትምህርት ትውልድን የመታደግ ልዩ ጥረት” ለዞን እና ለወረዳ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ በመካሄድ ላይ ነው። በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን የትምህርት ሥራ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ የወደቀ ዘርፍ መኾኑን አመላክተዋል።
የትምህርት ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠሩ ካሉ ችግሮች መካከል ቀዳሚው ደግሞ በክልሉ ያለው ግጭት መኾኑን ጠቁመዋል። ዛሬ ያልተማረ ትውልድ ተወዳዳሪ አይኾንም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በክልሉ የትምህርት ሥርዓቱ እንዲዛባ አቅዶ የሚሠራ ኀይል አለ ብለዋል። መምህራንን በማገት እና በማንገላታት፣ የመማር ማስተማር ሥራውን በማወክ ከዘመናዊነት ጋር የተጣላ አስተሳሰብ ለትምህርት ሥርዓቱ አደጋ ኾኗል ብለዋል።
“በትምህርት እጦት የተሠበረ ማኅበረሰብ ዘንድ የሚፈጠረው አደጋ አሁናዊ ብቻ ሳይኾን ዘመን ተሻጋሪ ነው” ብለዋል ዋና አሥተዳዳሪው። የትምህርት ሥርዓቱ የተጋረጠበትን አደጋ በቀጣይ ዓመት ለማስተካከል ሁሉም ባለድርሻ በትኩረት እንዲረባረብም ጥሪ አቅርበዋል። በመድረኩ የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ዓለምነው አበራ የዞኑን የትምህርት ሥራ አፈፃፀም ለውይይት አቅርበው ምክክር እየተደረገ ነው።
በመድረኩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የወረዳ አሥተዳዳሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ርእሰ መምህራን እና የትምህርት አመራሮች ተሳታፊ ኾነዋል።
ዘጋቢ፦ ጀማል ይማም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን