የታጠቁ ኀይሎች የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ የደንበጫ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

21

ፍኖተ ሰላም: ሚያዝያ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዞን እና የመከላከያ ሠራዊት መሪዎች በተገኙበት በሰላም እንጂ በጦርነት የለማ ክልልም፣ የተፈታ ችግርም የለም በሚል መሪ መልዕክት ከደንበጫ ከተማ እና ከደንበጫ ዙሪያ ወረዳ ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የውይይት መድረክ በደምበጫ ከተማ ተካሂዷል።

የጸጥታ ችግሩ ከተፈጠረ ጀምሮ በከተማ አሥተዳደሩ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶች መከሰታቸውን ያነሱት የደንበጫ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሙሉቀን መኮንን በተደጋጋሚ በተከናወኑ የሕዝብ ውይይቶች በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም ማስፈን መቻሉን ተናግረዋል። የጥፋት ኀይሎች እያደረሱ ያለውን ውድመት ማኅበረሰቡ በመረዳቱ ለሰላሙ መረጋጋት አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

በደንበጫ ከተማ አሥተዳደር የሰላም ሁኔታውን ከማረጋጋት ጎን ለጎን ማኅበረሰቡን በማሳተፍ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል። የምዕራብ ጎጃም ዋና አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ የጸጥታ ችግሩ በዞኑ ከፍተኛ የኾነ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ውድመት አድርሷል ብለዋል።

ግጭቱ ማኅበረሰቡ ማኅበራዊ እረፍት እንዲያጣ በማድረግ ለተወሳሰበ ችግር እየዳረገው ይገኛል ነው ያሉት። እየተካሄደ ያለው ግጭት የዞኑን ሕዝብ ታሪክ የማይመጥን አስነዋሪ ተግባር ነው ያሉት አቶ እድሜዓለም የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ለሰላም ዘብ በመቆም የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የደንበጫ ከተማ ነዋሪዎች በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ለተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች መዳረጋቸውን ተናግረዋል። አሁንም ቢኾን ከዚህ የከፋ ችግር ሳይከሰት እየደረሰ ያለውን ሁለንተናዊ ቀውስ በመረዳት የታጠቁ ኀይሎች የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ነዋሪዎች ጠይቀዋል። ለዚህ ደግሞ ሰላማዊ አማራጭ መከተል ብቸኛ መፍትሔ መኾኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ የምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዦችን ጨምሮ የዞን፣ የወረዳ አመራሮች እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ተገኝተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበደቡብ ወሎ ዞን በምርት ዘመኑ ከ15 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዷል።
Next article“በትምህርት እጦት በተሰበረ ማኅበረሰብ ዘንድ የሚፈጠረው አደጋ አሁናዊ ብቻ ሳይኾን ዘመን ተሻጋሪ ነው” የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ