
ደሴ: ሚያዝያ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን የ2017/18 የሰብል ልማት የንቅናቄ መድረክ የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት በደሴ ከተማ ተካሂዷል።
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አሕመድ ጋሎ እንደገለጹት በምርት ዘመኑ 432 ሺህ ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን መታቀዱን አንስተዋል። ከዚህም ከ15 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ነው የተናገሩት።
በዞኑ 12 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱ የተመላከተ ሲኾን 631 ሺህ ኩንታል ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ወደ ዞኑ ለማስገባት ታቅዷል።
በእቅድ ከተያዘው ሰው ሠራሽ የማዳበሪያ አቅርቦት ውስጥ 315 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ዞኑ የገባ ሲኾን 227 ሺህ ኩንታሉ ተሠራጭቷል ተብሏል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን የታቀደውን እቅድ ለማሳካት ቀዳሚ የሚኾነው በተግባቦት መሥራትን ነው ብለዋል። የምርት መጨመሪያ ፓኬጆችን ሳናንጠባጥብ መጠቀምም አለብን ሲሉ ተናግረዋል። የመፈፀም እና የማስፈፀም ብቃታችንም ከመቸውም ጊዜ በላይ ማደግ አለበት ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል።
የምርት ዘመኑን የሰብል ምርታማነት ግብ ለማሳካት ከዞን ጀምሮ በየደረጃው የጋራ መግባባት መፍጠር የተለያዩ የውይይት መድረኮችን እንደሚኖሩም ተጠቁሟል።
ዘጋቢ :- አበሻ አንለይ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን