“የዘመኑ አርበኝነት ድህነት እና ኋላቀርነትን ቀርፎ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

16

ባሕር ዳር: ሚያዚያ: 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 4ኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ፣ የጥናት እና ምርምር ውድድር መድረክ ተጀምሯል።

ዛሬ ሚያዚያ 27 ቀን የማንነታችን መገለጫና የጀግነንነታችን ማሳያ በሆነው “የዐርበኞች (የድል) ቀን” 4ኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ፣ የጥናትና ምርምር ውድድር መድረክን አስጀምረናል፡፡

መድረኩን ያስጀመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የክህሎት ልማት ለሀገራችን ዕድገት እና ብልፅግና ወሳኝ ነው ብለዋል። ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሠራናቸው ሥራዎች በፈጠራ የበሰሉ ብሩህ አዕምሮዎችን፣ የተፍታቱ እጆችን፣ በክህሎታቸው የበቁ ዜጎችን ለማፍራት አስችለዋልም ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ወራሪ ጠላትን መክተው ሉዓላዊነቷን ያስጠበቁ ጀግኖች አርበኞች እንደነበሯት ሁሉ፤ ዛሬ ደግሞ የሙያን እና የክህሎትን አቅም በመጠቀም ግብርናችንን የሚያዘምኑ፣ ለኢንዱስትሪ ዕድገት ወሳኝ መነሻ የኾኑ፣ የቱሪዝም ዘርፉን ውጤታማ የሚያደርጉ፣ ዲጂታላይዜሽንን የሚያፋጥኑ ብቁ ሙያተኞች አሏት ብለዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት “የዘመኑ አርበኝነት ድህነት እና ኋላቀርነትን ቀርፎ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው” ብለዋል።

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ደግሞ በየዓመቱ ከተለያዩ የሀገራችን ማዕዘን የመጡ ዜጎች ልምድ እንዲለዋወጡ፣ በተደመረ አቅም ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂና ምርምር ውጤቶችን እንዲያወጡ እያከናወነ ለሚገኘው ሥራ ላቅ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን ታሪክ ተጠቅሞ ሰላሙን በማስጠበቅ በልማቱ ሀገሩን ከፍ አድርጎ ማሳየት ይገባዋል።
Next articleበደቡብ ወሎ ዞን በምርት ዘመኑ ከ15 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዷል።