የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን ታሪክ ተጠቅሞ ሰላሙን በማስጠበቅ በልማቱ ሀገሩን ከፍ አድርጎ ማሳየት ይገባዋል።

13

ደብረ ታቦር: ሚያዝያ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 84ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን በደቡብ ጎንደር ዞን እና በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ተከብሯል። በዓሉ በደቡብ ጎንደር ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ እና በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት ነው የተከበረው።

ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችን እና አርበኞችን ጨምሮ በርካቶች በበዓሉ ታድመዋል። የደቡብ ጎንደር ዞን ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ጽሕፈት ቤት ሊቀመንበር አምባቸው ሞላ ኢትዮጽያ በጥንት ልጆቿ ተከብራ የኖረች ሀገር መኾኗን አንስተዋል። ሊቀመንበሩ የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን ታሪክ ተጠቅሞ የሀገርን ሰላም በማስጠበቅ በልማቱ ሀገርን ከፍ አድርጎ ማሳየት እንዳለበትም አሳስበዋል።

የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ በአንድነት መቆም እንደሚገባም ነው የተናገሩት። የደቡብ ጎንደር ዞን ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባል ወይዘሮ ማሬ ቀለሙ ከአርበኞች ሀገርን በወኔ እና በድል የመጠበቅ ታሪክን ለትውልድ ማስተላለፍን ወጣቱ ሊማር ይገባዋል ብለዋል። ወጣቱ የሀገርን ሰላም አንድ ኾኖ ማስጠበቅን ከአባቶች መማር እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት።

የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አለበል ደመላሽ 84ኛው የአርበኞች ቀን ሲከበር ያለፉትን መዘከር እንደሚገባ ጠቁመዋል። ትውልዱ ደግሞ የአባት አርበኞችን ፈለግ በመከተል የሀገርን ሰላም በማስጠበቅ ለልማት የተሰለፈ ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።

“ኢትዮጵያዊ የሰው የማይነካ የራሱን አሳልፎ የማይሰጥ ነው” ያሉት የደቡብ ጎንደር ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ወንዴ መሠረት የአሁኑ ትውልድም በልማት የበለፀገች ሀገርን በመገንባት የሀገርን ሰላም አስጠብቆ የአባቶችን ታሪክ በሥራ ሊገልጽ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን የአርበኞችን በዓል ማክበር የአባቶችን ታሪክ ለትውልድ ለማስተላለፍ ቁልፍ መኾኑን ተናግረዋል። ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን ታሪክ በሰላም እና በልማቱ በመድገም የኢትዮጵያን ከፍታ ማሳየት እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleማኅበረሰቡ ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክረ ሃሳብ በአግባቡ በመተግበር የወባ ተጋላጭነትን መቀነስ እንደሚገባ ተጠቆመ።
Next article“የዘመኑ አርበኝነት ድህነት እና ኋላቀርነትን ቀርፎ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ