
እንጅባራ: ሚያዝያ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ከተውጣጡ የሃይማኖች አባቶች እና ከወጣት አደረጃጀት ተወካዮች ጋር በወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ የተገኙ የሃይማኖት አባቶችም ወቅቱ ሰው ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ እንዳይሠራ ክልከላ የተደረገበት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች የማይደመጡበት ብሎም ሥርዓት አልበኝነት የነገሰበት መኾኑን ተናግረዋል።
ወጣቶች ለታሪክም ለነፍስም ከማይመች የእርስ በእርስ መጠፋፋት ታቅበው ለሰላማዊ ውይይት ቅድሚያ እንዲሰጡ የሃይማኖት አባቶቹ ጥሪ አቅርበዋል።
ቤተ ክርስቲያን ወጣቶችን በሥነ ምግባር የማነጽ እና ሰላምን የመስበክ የዘወትር ሥራዋን አጠናክራ ትቀጥላለችም ነው ያሉት።
የሃይማኖት አባቶችን ያወያዩት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የዋና ሥራ አሥፈፃሚ አማካሪ ግዛቸው ሙሉነህ በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ካደረሰው ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ባሻገር የማኅበረሰቡ የቆዩ እሴቶች እንዲሸረሸሩ ማድረጉን ተናግረዋል።
የሃይማኖት አባቶች በተዛባ ጎዳና የሚጓዙ ወጣቶችን የመምከር እና ሰላምን የማረጋገጥ ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባልም ነው ያሉት።
በመድረኩ የቅሬታ ምንጭ የኾኑ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ አቅርቦት እና የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ተነስተው በከተማ አሥተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሙሉጌታ ምህረት ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን