የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን የኃይል አቅርቦት ችግር በቅርብ ወራት ለመቅረፍ እየተሠራ መኾኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

29

አዲስ አበባ: ሚያዝያ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከገቡ ባለሃብቶች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ቡሬ እና አካባቢው ላይ የተገነባው የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በግብዓት እና በመሠረተ ልማት ተሟልቶ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንዲገባ ይፈለጋል ብለዋል።

በቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ካሉ 40 የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አሁን ላይ ሁለት ኢንዱስትሪዎች ብቻ በሥራ ላይ ያሉ መኾናቸውን ያወሱት ዶክተር አሕመዲን ሙሐመድ ሦስት ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ማሽን ገጠማ ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል። ቀሪዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሥራ አልገቡም ብለዋል።

የውይይት መድረኩ ዓላማም የኢንዱስትሪ ፓርኩን አጠቃላይ ሁኔታ በመረዳት በሙሉ አቅም ወደ ሥራ እንዲገባ ለማስቻል ነው ብለዋል። ችግሮችን በመለየት እና የመፍትሄ ሃሳቦችን በማስቀመጥ የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመሠረተ ልማት እና አቅም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አድማሱ ይፍሩ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንዲገባ መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በተለይም ከመብራት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር በጥቂት ወራት ውስጥ ይፈታልም ነው ያሉት። በመኾኑም ባለሀብቶች ከኀይል አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ስጋት በቀጣይ የሚቀረፍ በመኾኑ በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጁ መኾን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብርሃኑ ጣምያለው ቡሬ እና አካባቢው በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ትልቅ አቅም ካላቸው አካባቢዎች አንዱ መኾኑን አውስተዋል። ይሄን ታሳቢ በማድረግ ግብዓትን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር ለማስተሳሰር ፓርኩ እንደተገነባ ተናግረዋል።

ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንዲገባ ለማድረግ ይህ የውይይት መድረክ አስፈልጓል ብለዋል።

ዘጋቢ:- አዲሱ ዳዊት

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች የጎንጅ ቆለላ እና የአካባቢው ነዎሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
Next articleለዘላቂ ሰላም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ ሴቶች ተናገሩ።