
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ እና ሌሎችም የክልል እና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ መሪዎች በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በየደረጃው ያሉ አመራሮች ጋር እየተወያዩ ነው። ውይይቱ ወቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና የአገልግሎት አሰጣጥ ሥራዎችን የሚዳስስ ነው።
በተለይም የጎንደር ከተማ ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማትን በተመለከተ ሰፋ ያለ ውይይት እየተደረገ ነው። ውይይቱን የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መስፍን አበጀ (ዶ.ር) እየመሩት ነው።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ጎንደር በቀደመው ትውልድ ብልሃት እና ጥበብ የተሠራች ከተማ ናት ብለዋል። የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ቀደምቶች በጥበብ የሠሯትን ጎንደር ማደስ ብቻ ሳይኾን አዲስ የልማት ታሪክ የተሠራባትን ጎንደርን መፍጠር አለብን ሲሉ አሳስበዋል።
በተለይም ለከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች አዲስ እድል እና አደራ እጃቸው ላይ መውደቁን አቶ ይርጋ ገልጸዋል። መሪዎች ይህንን እድል ተጠቅመው ጎንደርን ለነዋሪዎቿ ምቹ በኾነ መልኩ የማልማት አደራቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በጎንደር ዙሪያ እየተከናወኑ ለሚገኙት ትልልቅ የልማት ሥራዎች መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል። እነዚህ የልማ ሥራዎች ዳር እንዲደርሱ እና ሌሎች አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲሠሩ ሕዝብን በማስተባበር ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው የጎንደርን ያረጀ ውበት እንደገና አድሶ እና በተጨማሪ የልማት ሥራዎች አጅቦ ጎንደርን ለመሞሸር እየተሠራ ስለመኾኑ ጠቁመዋል። ለዚህም መላ ኢትዮጵያውያን አሻራቸውን እያሳረፉ መኾኑን ከንቲባው ተናግረዋል።
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ውስጥ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችም ነዋሪዎችን ዘርፈ ብዙ አቅም በማስተባበር ለጎንደር ልማት እና ሰላም እየሠሩ ነው ብለዋል። ይህንን ተግባር የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን