
ደብረ ማርቆስ: ሚያዝያ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን ዕርቅ እና ሰላምን ለማምጣት ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች አንዱ የሽምግልና ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን ለመፍታት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
በኢትዮጵያ የእርቅ እና የሽምግልና ሥርዓት በሰዎች እርስ በእርስ ግንኙነት የሚከሰቱ አለመግባባቶችን የሚፈቱበት የቆዬ እሴት ቢኾንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ትኩረት እየተሰጠው አይደለም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች በዚሁ ሥርዓት መፈታት ሲገባቸው በተቃራኒው ግጭቶች ተባብሰው በመቀጠል ለሰው ሕይዎት መጥፋት፣ ለንብረት መውደም እና መሰል ውጥንቅጦች ምክንያት ሲኾኑ ይስተዋላል፡፡
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደብረ ማርቆስ ከተማ ወረዳ ቤተ ክህነት የትምህርት እና ሥልጠና ክፍል ኀላፊ መላከ ፀሐይ አሰፋ በሻህ እና በደብረ ማርቆስ ከተማ የእስልምና ጉዳዮች የሀገር ሽማግሌ የኾኑት እንድሪስ መሐመድ የሽምግልና ሥርዓት ዘመናትን የተሻገረ ጠቃሚ የኢትዮጵያውያን እሴት ቢኾንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ትኩረት እየተነፈገው ስለመምጣቱ ነግረውናል፡፡
መላከ ፀሐይ አሰፋ በሻህ ለሽምግልና ሥርዓታችን ዋጋ መስጠት እና የሀገር ሽማግሌዎችን ማድመጥ በእጅጉ አስፈላጊ መኾኑን ይናገራሉ፡፡ ሽምግልና ከቤት ይጀምራል የሚሉት መላከ ፀሐይ አሰፋ በሻህ መታረቅ ከአባቶች የተወረሰ እና መቀጠልም የሚኖርበት እሴት መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡
ባሕላዊ የእርቅ እና የሽምግልና ሥርዓት በወጉ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም የሚሉት ደግሞ አቶ እንድሪስ መሀመድ ናቸው። የሀገር ሽማግሌዎች በትብብር መንፈስ ለእውነት ቆመው ከሠሩ የማይፈታ ችግር አይኖርምም ብለዋል፡፡
የሽምግልና ሥርዓታችን አለመግባባቶችን በእርቅ እና በስምምነት ለመቋጨት ዓይነተኛ ሚና እንዳላቸው የሚጠቅሱት አባቶቹ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ትውልድን የመምከር ብሎም የማስማማት አባታዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡
ትውልዱ በበርካታ ዘመን አመጣሽ ነገሮች ሳይወሰድ ለባሕሉ እና ለወጉ ተገዥ ሊኾን ይገባል ያሉት አባቶቹ የሀገር ሽማግሌዎችን ማድመጥ እና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባም መክረዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን