
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 84ኛው የአርበኞች የድል ቀን በአዲስ አበባ 4 ኪሎ የድል ሐውልት በድምቀት ተከብሯል። የአርበኞች ድል መታሰቢያ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ የሚሰጠው መኾኑን የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ተናግረዋል።
ፋሺስት ጣሊያን በዓድዋ ጦርነት የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ሲል ከ40 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን ለመውረር ያደረገው ሙከራ የከሸፈው እና ድል የተመዘገበው በጀግኖች አርበኞች መስዋዕትነት እንደኾነ አስታውሰዋል። በወቅቱ የነበሩ ጀግኖች አባቶች በአርበኝነት ታግለው የሀገርን ነጻነት በመጠበቅ ለዚህ ትውልድ አስተላልፈዋል ያሉት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ይህ በመኾኑ ኢትዮጵያ ከነጻነት ቀን ይልቅ የድል ቀን በማክበር ላይ ትገኛለች ብለዋል።
የዚህ ዘመን ትውልድም የአባቶቹን የአርበኝነት መንፈስ በመውረስ ለመጪው ትውልድ የጸናች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ማስረከብ ይጠበቅበታል ነው ያሉት። በበዓሉ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ቀደምት እናትና አባቶቻችን ነጻነትን በደም አስከብረው ሀገር አውርሰውናል ብለዋል። በዚህም እንኮራለን፣ ቀደምት አርበኞች በከፈሉት ዋጋ ዛሬ ቀና ብለን በነጻነት አደባባይ እንድንራመድ አድርገውናል ነው ያሉት።
ነጻነታችን የተሟላ እንዲኾን እና ኢትዮጵያን ወደ ሁለንተናዊ እድገት ለማድረስ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች ማሸነፍ እና ድል ማድረግ ይገባል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ። ይህን የድል ቀን ስናከብር በአባቶቻችን ታሪክ በመኩራራት ብቻ ሳይኾን በዘመናችን የሚታወስ ድል በማስመዝገብ መኾን አለበት ነው ያሉት።
የስንፍና ፖለቲካን ለመረጡ ኀይሎችም ጀግንነት በሰላሚዊ መንገድ የሚገለጥ በመኾኑ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ለሀገር እድገት እና ለለውጥ በጋራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል። ሀገር የምትጸናው በአብሮነት እና በመተሳሰብ በመኾኑ ሁላችንም ለለውጥ እና ለስኬታማ ድል በጋራ ልንቆም ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን