
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ለ2 ሺህ ዓመታት ያህል የተደጋገመ የወረራ ሙከራ እንደተደረገባት የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በአውሮፓ፣ በእስያ እና በአፍሪካ የተነሱ መንግሥታት ግዛታቸውን ሲያስፋፉ በነበሩበት ጊዜ ኢትዮጵያንም ለማስገበር ብዙ ጊዜ ሞክረዋል።
ከቀደምቶቹ መካከል ደግሞ የግሪክ ንጉሥ “ታላቁ አሌክሳንደር” ተጠቃሽ ነው። ንጉሱ ግዛቱን በማስፋፋት እስከ ግብጽ እና ሕንድ ድረስ አስገብሯል። ከግብጽም አልፎ ኢትዮጵያንም ለመውረር አቅዶ እንደ ነበር ይነገራል። ይሁን እንጅ ስለ ኢትዮጵያውያን ጀግንነት ቀድሞ ሰምቶ ስለነበር ጦርነቱን ለማካሄድ አልደፈረም። ንጉሱ ስለ ኢትዮጵያውን የተነገረው ጀግንነት እውነት ስላልመሰለው አሉኝ ከሚላቸው የጦር አለቆች ጋር በመኾን ተራ ሰው በመምሰል ለስለላ ወደ ኢትዮጵያ ገባ ይላል ታሪኩ።
ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን የሰማችው የወቅቱ የኢትዮጵያ ንግሥት ሕንደኬም ወደ ቤተ መንግሥት አስጠርታ “ዓለምን አንቀጥቅጠህ የገዛህ ታላቁ እስክንድር ኾይ ዛሬ በሴት እጅ ተይዘሃል” ስትለው ደንግጦ ጥበቧን በማድነቅ እና ሕዝቡም በጦር የማይፈታ መኾኑን ተናግሮ እንዳልተሳካለት ይነገራል።
ኢትዮጵያን ለማስገበር ከተነሱ የአውሮፓ ነገሥታት መካከል ሌላኛው የሚጠቀሰው የሮማው አውጉስቶስ ቄሳር ነው። አውግስቶስ ቄሣር በአውሮፓ፣ በአፍሪካ እና ኤዥያ የሚገኙ በርካታ ሀገራትን ተቆጣጥሮ ካስገበረ በኋላ “አይሎስ ጋሎስ” በሚባል የጦር አዛዥ የሚመራ በ10 ሺህዎች የሚቆጠር እግረኛ እና ፈረሰኛ ጦር በግብጽ እና በሱዳን በኩል አድርጎ የአክሱምን መንግሥት ለመውጋት ገሰገሰ።
ይህንን የሰሙ ኢትዮጵያውያን ቀድመው ተዘጋጅተው ወደ ኢትዮጵያ ሳይገባ ገጠሙት። ለዓመታት በቆየው ውጊያ የቄሳሩ ጦር እየተመናመነ በመምጣቱ የጦር አዛዡ ከሮማው ንጉስ በታዘዘው መሠረት ጦርነቱ በእርቅ አልቆ የተረፈውን ወደ ሀገሩ ይዞ ተመለሰ። እንግዲህ የጣሊያን ትንኮሳ በዋናነት ከዚህ የጀመረ ይመስላል።
በአውጉስቶስ ቄሳር የደረሰውን ሽንፈት ብድር ለመመለስ በ54 ዓ.ም በሮማ ነግሶ የነበረው ንጉስ ኔሮ ለወረራ ተነሳ። የኔሮ አማካሪዎችም ኢትዮጵያውያን በጦርነት የማይሸነፉ መኾናቸውን ነገሩት። ወደ ኢትዮጵያ ጦር መላክም ትርፉ ውርደት መኾኑን አስጠነቀቁት። ኔሮ የአማካሪዎቹን ምክር ቢሰማም የዘመኑን የኢትዮጵያ ጦር የሚሰልል ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ላከ። “ኔሮ የአባቶቹን ምኞት ለመፈጸም የዓባይን ምንጭ የሚፈልጉ ናቸው ብሎ ለኢትዮጵያ ንጉሥ ደብዳቤ ጽፎ ሰላዮቹን ወደ ኢትዮጵያ ላከን። የተላክነው ሰላዮች ኢትዮጵያ ውስጥ ከርመን ስንመለስ ሕዝቡ ጦረኛ መኾኑን እና ወደ ኢትዮጵያ ጦር መላክ እንደማያዋጣ ነገርነው፤ ሀገሪቱ ግን እጅግ ለም ናት አልነው” ሲል ከስለላ ቡድኑ ጋር አብሮ የነበረው “ሴኔካ” የተባለው የታሪክ ጸሐፊ ማስፈሩ ይነገራል።
የተነገረውን አልሰማ ያለው ኔሮ ኢትዮጵያን ማስገበር እንደሚችል ተማምኖ “ካምቤይስ” በሚባል የጦር መሪ የሚመራ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ልኮ ድል ተመትቶ መመለሱን የታሪክ ጸሐፊዎቹን “ዲዩ ካሲዮ” እና “ፕሊኒን” ጠቅሰው ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያ እና የኢጣሊያ ጦርነት በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ አስፍረውታል።
በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት ስምምነት ላይ የደረሱበት ወቅት ነበር። በዚህ ወቅም ጣሊያኖች ሀገራቸውን ወደ ጥንቱ የሮማ አገዛዝ ለመመለስ ተነሱ። ጣሊያን ህልሟን ለማሳካት የተሻለ እና ምቹ ኾኖ ያገኘችው ደግሞ ከቀይ ባሕር – ሕንድ ውቅያኖስ እስከ ዛንዚባር ድረስ ያለው አካባቢ ነው።
በአያቶቻቸው ያልተሳካውን ኢትዮጵያን የማስገበር ሕልም ለማሳካት በሃይማኖት ሰበብ በአባ ጁሴፔ ሳፔቴ አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ከአሰብ ባላባቶች ጋር ተወዳጁ። በ1862 ዓ.ም ከባላባቶቹ “ለማረፊያ” በሚል መሬት በመግዛት “ሩባቲኖ” የሚባል የኢጣሊያ የመርከብ ኩባንያ ወደብ እንዲመሠርት አደረጉ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ የነበሩት አጼ ተክለጊዮርጊስ ከአጼ ቴዎድሮስ ያልተረጋጋች ሀገር ተረክበው ስለነበር ጉዳዩን ያሰቡበት አይመስልም።
ኩባንያው አሰብን ለ12 ዓመታት ከተጠቀመበት በኋላ በ1874 ዓ.ም (በአጼ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት) ለጣሊያን መንግሥት ሸጠው። በዚሁ ዓመት የኢጣሊያ መንግሥት አሰብ የጣሊያን ግዛት መኾኑን በአዋጅ አሳወቀ። ከዚህም ባለፈ በምጽዋ ጦር በማስፈር ወደ መሀል በመስፋፋት ለጦርነት መዘጋጀት ጀመሩ፡፡
ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ራስ አሉላ ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም በእምቢተኝነታቸው ጸኑ። በድርጊታቸው የተቆጡት ራስ አሉላ ሰሐጢ ላይ ጣሊያንን ድል አደረጉ። በዚህ የተበሳጩት ጣሊያኖች ተጨማሪ ጦር በመላክ ሊያጠቁ ተሰናዱ፡፡ ይሄን የተረዱት ራስ አሉላ ወደ ኋላ ተመልሰው በቆረጣ በኮሎኔል ቶማስ ዲክሪስቶፎሮስ እየተመራ የመመጣውን የጠላት ጦር ዶጋሌ ላይ በከበባ ዶግ አመድ አደረጉት። ይህንን እልቂት ራሳቸው ጣሊያኖች “የዶጋሌ እልቂት” እያሉ እንደሚጠሩት የታሪክ ጸሐፍት ከትበውታል።
ዶጋሌ ላይ ድል የተመታው የጣሊያን መንግሥት ቀን ቆጥሮ በ1888 ዓ.ም የሀገሪቱን ድንበር ጥሶ በድጋሜ ወረራ ፈጸመ። ኢትዮጵያውያንም በጀግንነት በመፋለም በድል አጠናቀቁ። ድሉ ከጣሊያን መንግሥት ባለፈ የአውሮፓ መንግሥታትን ጭምር ጭንቀት ውስጥ ከተተ። ሽንፈቱ የነጭ ሽንፈት እንደኾነ ተገነዘቡ።
ድሉን ተከትሎ “ኢትዮጵያ የግዛት ማስፋፋት ልታስብ ትችላለች” በሚል የብዙ ቅኝ ገዥ ሀገራትን ትኩረት መሳብ ቻለ። ሀገሪቱንም በሰሜን እና በደቡብ ምሥራቅ ጣሊያን፣ በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ እንዲሁም በምሥራቅ ፈረንሳይ ከበባ ማድረጉን ቀጠሉ። በተለይም ደግሞ ጣሊያን በዓድዋ የገጠማትን የሽንፈት ቁስል በድል ለመሻር ሀገሪቱን ለመምራት ወደ ሥልጣን የመጡት ሁሉ እንቅልፍ ነሳቸው። በ1922 ወደ ሥልጣን የመጣው ፋሽስቱ ሞሶሎኒም እረፍት አልነበረውም።
በ1927 ዓ.ም ጣሊያን በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1908 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገውን የወሰን ስምምነት በማፍረስ 96 ኪሎ ሜትር የኢትዮጵያ ግዛት ላይ በሚገኘው ዋርዴር እና ወልወል ላይ ጦሯን አሰፈረች። ሳትውል ሳታድር በአካባቢው በነበረው በኢትዮጵያ ጦር ላይ ጦርነት ከፈተች። ከዚህም ባለፈ የጣሊያን ጦር መስከረም 1928 የመረብን ወንዝ ተሻግሮ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ጭምር ወረራ ፈጸመ።
የኢትዮጵያውያ አርበኞችም ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የጣሊያን ጦር በአጸፋዊ ምላሽ እረፍት አሳጡት። ትግሉ ከአምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ የኢትዮጵያ አርበኞች በከፈሉት መስዋዕትነት በድጋሜ ድል ማድረግ ተችሏል፡፡ ቀኑ የኢትዮጵያ አርበኞች በአንድነት በፋሽስቱ ጣሊያን ዳግም ወረራ ወቅት የከፈሉትን መስዋዕትነት እና ያስገኙትን ድል ለማሰብ በየዓመቱ ሚያዝያ 27 ቀን ይከበራል፡፡
ለዛሬው የጣሊያንን ተደጋጋሚ ወረራ አነሳን እንጅ ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ቱርኮች፣ ግብጾች፣ ማህዲስቶች እና በጎረቤቶቿ ጭምር የተቃጣባትን ትንኮሳ በተባበረ የኢትዮጵያውያን ክንድ ድል በማድረግ ነጻነቷን ያስጠበቀች ቀደምት ሉዓላዊት ሀገር ያደርጋታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን