ወጣቱ ትውልድ ከአባት አርበኞቹ ጽናትን እና አንድነትን ሊማር እንደሚገባው ተጠቆመ።

15

ሰቆጣ: ሚያዝያ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፋሽስት ኢጣሊያ በ1888 ዓ.ም በዓድዋው ጦርነት የሽንፈት ጽዋን ከተጎነጨች በኋላ ለአርባ ዓመታት ያክል በበቀል እያዘጋጀች ጊዜ ስትጠብቅ ቆይታለች። በዚህም ከ1927 እስከ 1933 ዓ.ም ባሉት አምስት ዓመታትም ድጋሜ ኢትዮጵያን በመውረር በዓለም አቀፍ የጦር ሕግ የተከለከሉ መርዛማ ኬሚካሎችን ሳይቀር ተጠቅማ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ሞክራለች።

ምንም እንኳ ሙከራው ባይሳካም ለ40 ዓመታት ያክል እንድትዘጋጅ ያደረጋትም በዓድዋ የቀመሰችው መራራ ሽንፈት በአውሮፓውያኑ ተቀባይነቷን እንድታጣና የነጮችን የበላይነት ቀንሰሻል ከሚለው ትችት ለመውጣት አስባ እንደኾነ በሰቆጣ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የታሪክ መምህሩ ክብረት ተስፋዬ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ያገኙትን ድል ድጋሜ ለማስቀጠል ያለመታከት እና ያለተስፋ መቁረጥ ታግለው ድጋሜ ድል ማድረጋቸውን የገለጹት የታሪክ መምህሩ የአሁኑ ትውልድም በድህነት ላይ ታሪክ ለመሥራት ያለመታከት ሊያለማ ይገባል ነው ያሉት።

የጣሊያንን አስከፊ ወረራ ለመመከት እንደ ዓድዋው የተደራጀ ኀይል ባይኖርም አባት አርበኞች በየአካባቢያቸው የመጣውን የፋሽስት ጦርን እየለቀሙ በአንድነት እና በጽናት ለአምስት ዓመታት ተዋግተው ድል ማድረጋቸውን በዋግ ኽምራ ፖሊስ መምሪያ የአካባቢ ሰላም ማስከበር ክፍል ኀላፊ ምክትል ኮማንደር ደሳለኝ ዓለሙ አንስተዋል።

ዛሬም ወጣቱ ትውልድ የጀግኖች አርበኞችን የድል መታሰቢያ ቀንን ሲያክብር የአካባቢውን ሰላም በማጽናት እና በመጠበቅ ሊኾን እንደሚገባ ምክትል ኮማንደሩ አሳስበዋል። ወጣት መንግሥቱ መሠረት አባቶቻችን በደማቸው ያጸኗትን ሀገር የመጠበቅ እና ሰላሟን የማጽናቱ ኀላፊነት በወጣቱ እጅ ላይ ነው፣ ይህንን ኀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ደግሞ ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።

እንደሀገርም፣ እንደ ክልልም ከገባንበት ግጭት መላቀቅ የምንችለው ወጣቶች ጦርነትን የተጠየፍን ልማት እና ሰላምን ወዳዶች ስንኾን ብቻ ነው ያለችው ደግሞ ወጣት በላይነሽ ግርማ ናት። አባት አርበኞች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጾታ ሳይለያዩ ሀገርን እንዳቆዩን ሁሉ በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት ሳንለያይ ልንጠብቃት ይገባል ብላለች።

ለ84ኛ ጊዜ ለሚከበረው የአርበኞች የመታሰቢያ የድል ቀንም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

Previous articleየኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በድል ሐውልት የአበባ ጉንጉን አስቀምጡ።
Next article“በኢትዮጵያ ላይ የተደረጉ ተደጋጋሚ ወረራዎች እና የአልደፈርባይነት ተጋድሎ”