
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎችም የአማራ ክልል እና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ መሪዎች ከወገራ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል። ከፍተኛ መሪዎች ከገደብየ፣ ይሳቅ ደብር፣ ኮሶየ፣ የአምባ ጊዮርጊስ ዙሪያ እና ሌሎችም የአካባቢው የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች ጋር ነው የተወያዩት።
ውይይቱ “ዘላቂ ሰላም ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ መልዕክት የተካሄደ ሲኾን እንደ ክልል እና በአካባቢውም ገጥሞ የቆየውን የጸጥታ ችግር መነሻ ለመነጋገር፣ አሁን የተገኘውን ሰላም የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ እና በሙሉ አቅም ወደ ልማት ለመግባት ያለመ ነው።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ የወገራ ሕዝብ የክልሉን እና የሀገርን ሰላም ለማስከበር ሲል ከመሪዎቹ ጋር በመቆም ዋጋ የከፈለ ነው ብለዋል። እንደ አማራ ክልል የሚያነሳቸው የመልማት እና የፍትሕ ጥያቄዎች ያሉት፤ ጥያቄዎቹንም አንዳንዶቹን ያስመለሰ፣ ቀሪዎችን ደግሞ በሕግ እና በስክነት ለማስመለስ የሚሠራ ሕዝብ መገኛ አካባቢ መኾኑንም ተናግረዋል።
የሕዝብ ጥያቄ ይሄው ኾኖ እያለ ጥያቄውን አስመልሳለሁ በሚል ሰበብ ሰላምን የሚያደፈርስ፤ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን የሚያስቆም ታጣቂ ተፈጥሯል ነው ያሉት። ሕዝብ ትምህርት ቤት እንዲሠራለት ይጠይቅ ነበር፣ መንግሥትም ባለው አቅም ጥያቄዎችን ለመፍታት ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ጥረት ላይ ነው፤ ይሁን እንጅ ነባር ትምህርት ቤቶች በኀይል እንዲዘጉ መደረጉን አንስተዋል። “የትምህርት ቤት በሮችን በአፈሙዝ ዘግቶ ትውልድን ለድንቁርና ማጨት በፍጥነት ሊቆም ይገባል” ሲሉም አሳስበዋል።
ሕጻናት እና አረጋውያን ጭምር ታግተው የሌላቸውን ገንዘብ እንዲከፍሉ ሲጠየቁ፣ መክፈል ያቃታቸው በጠራራ ፀሐይ በግፍ ሲገደሉ ይህ ሕገ ወጥ ድርጊት ከአካባቢው ማኅበረሰብ እንዴት ሊሰወር ቻለ ሲሉም ጠይቀዋል ኀላፊው።
ሕዝቡ ከሕዝብ የሚጠበቀውን ነገር ማድረግ አለበት፣ በውስጡ ተሰግስገው ሕገ ወጥ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ አካላትን በመጠቆም ለጸጥታ አካላት አጋልጦ መስጠት አለበት ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
አርሶ አደሮች ለሰላማቸው እና ለልማታቸው መቆም አለባቸው፣ የሌላቸውን እየጠየቀ የሚያስቸግራቸውን አካል በጋራ ኾነው መምከር እና ማስተካከል፤ አልኾን ካለም ከጸጥታ አካሉ ጎን በመቆም አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ አለባቸው ነው ያሉት።
የሃይማኖት አባቶች ሰላምን በመስበክ እና የመንፈስ ልጆቻቸውን ለሰላም፣ ለፍቅር እና ለበጎ ነገር ሁሉ በማሰለፍ ደጉን ሕዝብ ከችግር የማውጣት አባታዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አቶ ይርጋ ጠይቀዋል።
አርቆ አሳቢ ወጣቶች ራሳቸውን ከአልባሌ ነገር በማራቅ እና ከሀገር መጋቢ አርሶ አደሮች ጎን ቆሞ አይዞህ በማለት ይህንን የችግር ጊዜ ማሳለፍ እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመንግሥት ፍላጎት ድህነት እና ኋላቀርነት ተወግዶ ያደገች ሀገር፣ ሰላም ኾኖ የሚያመርት ዘመናዊ አርሶ አደር እና ሰላሙ የተጠበቀ ሕዝብ መፍጠር ነውም ብለዋል ኀላፊው።
መንግሥት ያለውን በቂ የጸጥታ ኀይል በየአካባቢው አሰማርቶ ሰላምን የማረጋገጥ ኀይል አለው፤ ይህ ግን ጦርነት ነውና ኪሳራ ያስከትላል፤ አርሶ አደሩንም ተረጋግቶ እንዳያለማ ያደርጋል ነው ያሉት።
ይልቁንም ሰላምን ምርጫ በማድረግ የሰላም ጥሪዎች እየተደረጉ ነው፤ የታጠቁ ኀይሎች ሁሉ ፈጥነው ወደ ሰላም በመመለስ ሕዝባቸውን በልማት ይካሱ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን