በተኪ ምርቶች 3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናገሩ።

43

አዲስ አበባ: ሚያዝያ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 3ኛው “የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ” በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተከፍቷል።

በመርሐ ግብሩ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ያለ ኢኮኖሚ ዕድገት የጸና ሀገር ሊኖር አይችልምና የኢንዱስትሪ ዘርፉን ማዘመን ተገቢ ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ለስንዴ እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ሲወጣ እንደነበር ገልጸው አሁን ላይ በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል ብለዋል። ይህ ደግሞ አምራች ኢንዱስትሪው የግብርናውን ዘርፍ መደገፍ ስለቻለ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

አምራች ኢንዱስትሪው ለውጭ ኤክስፖርት አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል። ባለፈው ዓመት የቡና ምርትን ወደ ውጭ ኤክስፖርት በማድረግ 1 ነጥብ 4
ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ዘንድሮም ከቡና ብቻ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል። ግብርና የዕድገት ምሰሶ መኾን የቻለው አምራች ኢንዱስትሪው ድልድይ ስለኾነ ነው ብለዋል።

ወርቅ ወደ ውጭ በመላክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በቱሪዝም ዘርፉም እንደ ሀላላ ኬላ፣ ላሊበላ፣ የፋሲል አብያተ መንግሥታት፣ የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት እና ሌሎች ቅርሶች ዘመኑን በዋጀ መንገድ እንዲታደሱ አምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ነው ያሉት። በዚህም በበጀት ዓመቱ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፉ ከአፍሪካ ቀደሚ መኾን ችላለችም ብለዋል።

በቴክኖሎጂ ዘርፉም አርቴፌሻል ኢንተልጀንስ፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና ፋይዳን ለመተግበር የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት አምራች ኢንዱስትሪው የማምረት አቅም 46 በመቶ ነበር አሁን ላይ 61 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት።

ባለፉት ዓመታት የተዘጉ እና አቁመው የነበሩ 830 የኢንዱስትሪ ፋብሪካዎች መልሰው ሥራ እንዲጀምሩ እና ምርታማነት እንዲያድግ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ1 ሚሊዮን እስከ 90 ሚሊዮን ወጨ የተደረገባቸው 13 ሺህ 800 መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች አሁን ላይ ሥራ ጀምረዋል ብለዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከውጭ የሚገባን ምርት በሀገር ውስጥ በመተካት 3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ማስቀረት መቻሉንም አንስተዋል።

አምራች ኢንዱስትሪው የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕውን ለማድረግ ከፍተኛውን ድርሻ እየተወጣ ስለመኾኑም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው በዘርፉ የሚያጋጥሙ የማምረቻ ቦታ፣ የፋይናንስ ችግር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ባለድርሻ አካላት በርብርብ እንዲሠሩም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ” ባለፉት ሦስት ዓመታት ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ተናገሩ።
Next article“ኢትዮጵያ ታምርት” ወይም ‘Made in Ethiopia’ ኤክስፖ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት ተከፈተ።