“በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ” ባለፉት ሦስት ዓመታት ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ተናገሩ።

41

አዲስ አበባ: ሚያዝያ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 3ኛው “የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ” በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተከፍቷል።

በኤክስፖው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበልን ጨምሮ ሌሎች የክልል እና የፌደራል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች፣ የምግብና የእንጨት ሥራ ውጤቶች፣ ኬሚካልን ጨምሮ ልዩ ልዩ የኢንዱስትሪ ምርቶች በኤክስፖው መቅረባቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ተናግረዋል።

“የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ጥራት ያላቸው ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተጀመረ መርሐ ግብር መኾኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸው እንዲጎለብት ማድረጉንም አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል። ሥራ አቁመው የነበሩ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።

ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ተኪ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ከማቅረብ ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ አምራች ዘርፉ እንዲነቃቃ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

የተለያዩ ምርቶችን በዓይነት፣ በጥራት እና በብዛት በማሳደግ በኤክስፖው ማቅረብ መቻሉን ሚኒስትሩ አንስተዋል።

የኤክስፖው ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን ምርቶች ማስተዋወቅ፣ ተጨማሪ የገበያ ዕድሎችን ማስፋት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የልምድ ልውውጥ መፍጠር፣ የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆ መፍታት፣ ፈጠራን ማበረታታት፣ የፈጠራ ውጤቶች ገበያ እንዲያገኙ ማስቻል፣ የምርት ጥራትን ማሻሻል ነው ብለዋል።

“በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ” ባለፉት ሦስት ዓመታት ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ሚኒስትሩ መላኩ አለበል አረጋግጠዋል።

በኤክስፖው ከ280 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ይሳተፋሉ፤ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይትም ይፈጸማል ተብሎም ይጠበቃል።

የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት ኤክስፖው ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ይቆያል ተብሏል። ከ120 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ዜጎች ይጎበኙታል ተብሎም ይጠበቃል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleከ10 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የህክምና መሳሪያዎች እና መድኃኒቶች መሠራጨታቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
Next articleበተኪ ምርቶች 3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናገሩ።