የዓለም ባንክ ለኬንያ የአንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አደረገ፡፡

140

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) የዓለም ባንክ የኬንያ የበጀት ጉድለት ለመሙላት የአንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የብድር ድጋፍ ማጽደቁ ተገለጸ፡፡

የኬንያ ባለስልጣናትን ዋቢ አድርጎ ሲጂ ቲ ኤን እንደዘገበው ባንኩ ዛሬ ነው ለኬንያ የሚሰጠውን ድጋፍ ያጸደቀው፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ የኬንያን የበጀት ጉድለት ወደጥቅል ሀገራዊ ምርት (ጂ ዲ ፒ) 8 ነጥብ 2 በመቶ ደረጃ አሳድጎታል፡፡ በእርግጥ አስቀድሞ የነበረው ትንበያ እስከ 7 በመቶ ጉድለት ሊያጋጥም እንደሚችል ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የግብር አለመሰብሰብ፣ ከውጭ በሚገቡ ላይ የሚጣል የተጨማሪ እሴት ታክስ መቋረጥና መሰል በወረርሽኙ ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች ናቸው፡፡

የዓለም ባንክ የኬንያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት በዓመቱ መጀመሪያ ከታቀደው 5 ነጥብ 4 በመቶ ወደ 1 ነጥብ 5 በመቶ እንደሚወርድ ትንበያ አስቀምጧል፡፡ የኬንያ መንግሥት ግን ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 በመቶ ዕድገት እየጠበቀ ነው፡፡

የዛሬው የዓለም ባንክ የብድር ድጋፍ ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት 739 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ካደረገ ከሁለት ሳምንት በኋላ የተገኘ ሌላ አዲስ ዕድል ተብሏል፡፡

ኬንያ 963 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን አረጋግጣለች፤ ከእነዚህ ውስጥ የ50ዎቹ ሕይወት አልፏል፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ
በአብርሃም በዕውቀት

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበጂቡቲ 117 ሰዎች አዲስ በቫይረሱ መያዛቸው ተገለጸ፡፡
Next articleበግሪክ ማላካሳ የስደተኞች ካምፕ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ደቅኗል፡፡