
ደብረ ብርሃን: ሚያዝያ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጤና ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ አስታውቋል።
የመምሪያ ኀላፊው በቀለ ገብሬ በሁሉም ጤና ተቋማት መድኀኒቶች በበቂ ኹኔታ ለማቅረብ በሕጋዊ መንገድ የግዢ አማራጭ በመጠቀም እንዲሟሉ እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ በሚገኙ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የማኅበረሰብ መድኀኒት ቤቶችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከክልሉ መንግሥት እና ከአጋር አካላት የተገኘን ሀብት በአግባቡ ለጤና ዘርፍ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
የመድኃኒት፣ የህክምና መሳሪያ አቅርቦቶች እና ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ መሳሪያዎችን ማሟላት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከ10 ነጥበ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው ልዩ ልዩ የሕክምና መሳሪያዎች እና መድኃኒቶች ተሠራጭተዋል ነው ያሉት።
በ43 ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት አገልግሎት ለመስጠት ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉንም ጠቅሰዋል።
የተሰራጩት መድኃኒቶች በፍትሐዊነት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እንዲኾኑ ለማስቻልም በየወረዳው እና በከተማ አሥተዳደሮች የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት ለማቋቋም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት እጥረት እንዳያጋጥም ከኢትዮጵያ መድኀኒት አቅራቢ ድርጅት በተጨማሪ ሜዴክስ ዲያኖስቲክ ሴንተር ከተባለ የመንግሥት ልማት ድርጅት ጋር መድኃኒት የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ መኸኑንም ኀላፊው ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ስንታየሁ ኃይሉ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን