የመማር ማስተማሩ ውጤታማ እንዲኾን እየተሠራ ነው።

20

ደብረ ታቦር: ሚያዝያ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በደብረ ታቦር ከተማ አካሂዷል። በመድረኩም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የነበሩ ክፍተቶች እና ጥንካሬዎች ተነስተዋል። ያለው የጸጥታ ችግር በመማር ማስተማሩ ላይ ችግር መፍጠሩ በተሳታፊዎች ተነስቷል።

ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተጋገዝ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማፋጠን እየሠሩ መኾኑን ነው ተሳታፊዎች የተናገሩት። በምክክር መድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ የአማራ ክልል ሕዝብ አጋጥሞት የማያውቅ ችግር እንዳጋጠመው ገልጸዋል።

ችግሩም ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ የፈጠረ እንደኾነ ነው የተናገሩት። የሰላም እጦቱ የትምህርቱን ዘርፍ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረበትም ተናግረዋል። ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ በውይይት እና በመነጋገር መፍታት፣ ታሪካችንን መገንባት እና እያረምን መሄድ ይገባል ነው ያሉት።

ሁሉም አሸናፊ የሚኾነው በሰላም ነው” ያሉት አቶ በሪሁን በአማራነት ስም የሚቀልድ ቡድን ሊኖር አይገባም ብለዋል። በመደጋገፍ እና በመመካከር ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት። የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደስታ አስራቴ የትምህርት ሥርዓቱ በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዳ ያለ ዘርፍ እንደኾነ ተናግረዋል።

በችግር ውስጥ ኾኖም ግን መማር ማስተማሩን ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመሥራት ማስቀጠል እንደተቻለ ተናግረዋል። እየደረሰ ያለው ጥፋት እና ችግር ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ሙሉ በሙሉ እንዳይገኙ አድርጓቸዋል ብለዋል። ችግሩን ለመሻገርም በሦስት ዙር የተከፈለ የምዝገባ ሂደት ተግባራዊ ተደርጓል ነው ያሉት።

በዚህም ከትምህርት ገበታ ዘግይተው የመጡ ተማሪዎችን በማገዝ እንዲኹም መድረኮችን አዘጋጅቶ በማወያየት መማር ማስተማሩን ማስኬድ ተችሏል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“በሕዝብ ጥያቄ ሰበብ ሕዝብን መበደል ሊቆም ይገባል” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next articleከ10 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የህክምና መሳሪያዎች እና መድኃኒቶች መሠራጨታቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።