
ጎንደር: ሚያዝያ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የገጠር ቀበሌዎች ተገኝተው ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በሰላም እና በልማት ሥራዎች ዙሪያ ተወያይተዋል። በውይይቱ ላይ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ እና ሌሎችም የክልል እና የዞኑ መሪዎች ተገኝተዋል።
መሪዎች በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች ከሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ነው የተወያዩት። የጭንጫየ፣ ባሕሬ ግንብ እና ምንዝሮ የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል። ውይይቱ የጎንደር እና የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት በመመለስ በሙሉ አቅም ወደ ልማት ለመግባት የሚያስችል ነው።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ የጎንደር ሕዝብ ሀገርን ጠብቆ በማቆም በኩል የካበተ ልምድ ያለው፤ ለእርቅ እና ለሰላምም ቀናዒ ነው ብለዋል። አኹን ግን ከዚህ ሕዝብ ባሕል እና እሴት ውጭ የኾኑ የጥፉት ቡድኖች ከወዲያ ወዲህ እየተላላኩ ሕዝቡን ከልማት ለመነጠል እና ለማሰቃየት እየተንቀሳቀሱ መኾኑን አመላክተዋል።
ይህ አካሄድ ለጎንደር ሕዝብ የተጀመሩ ትላልቅ የልማት ሥራዎችን ወደኋላ የሚያስቀር፣ የክልሉንም ተወዳዳሪነት የሚያዳክም ነው ብለዋል። የክልሉ ሕዝብ በተለይም አርሶ አደሮች የዳበረ የሰላም ምክረ ሀሳብ እና የእርቅ እሴት ባለቤቶች ናቸው፤ አኹንም ቢኾን አጥፊውን አካል በመምከር ወደ ሰላም መመለስ የሁሉም ኀላፊነት ነው ብለዋል።
የጽንፈኛ ቡድኑን እኩይ ተግባር ሁሉም በውል ተረድቷል፣ ይህ ቡድን ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ዕውነትን ደፍሮ መናገር እንደሚገባም አቶ ይርጋ ተናግረዋል። ኀላፊው እንዳሉት አርሶ አደሮች ዓላማ በሌለው ታጣቂ ቡድን ለሁለት ዓመታት ሙሉ በደል እና እንግልት ሲደርስባቸው ቆይቷል። የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ተዘርፈዋል፤ የጠላትን ሀሳብ የተሸከሙ አካላት ንጹሀንን ሲዘርፉ፣ ሲያግቱ፣ ሲገድሉ እና መውጫ መግቢያ ሲዘጉ ቆይተዋል።
እነዚህ አካላት ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አርሶ አደሮች በጋራ ቆመው ለእውነት ሊታገሉ እንደሚገባም አቶ ይርጋ መልዕክት አስተላልፈዋል። በደል እና እንግልትን እያወቁ ችሎ ዝም ማለት የበለጠ ዋጋ ያስከፍላል፤ ስለዚህ ለእውነት ሲሉ መስዕዋትነት እስከመክፈል መቆም እና ጥፋተኞችን ማረም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት መሠረታቸው ሰላም ነው ብለዋል አቶ ይርጋ። የሃይማኖት አባቶች እንደ የሃይማኖታቸው ትክክለኛውን የሰላም እና የአብሮነት በር በስብከቶቻቸው ማሳየት፤ ሰላምን ከሚያውክ አልባሌ ንግግር መቆጠብ እና አባታዊ ኀላፊነትን ከሚያስዘነጋ ዝምታ መውጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በሕዝብ ጥያቄ ሰበብ ሕዝብን መበደል ሊቆም ይገባልም ብለዋል አቶ ይርጋ። የመጀመሪያው የሕዝብ ጥያቄ ሰላም ነጻነት እና ልማት ነው፤ የመንግሥትም ፍላጎት እና አቋም ሕዝቡ በነጻነት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ እንዲሠራ፣ ማኅበራዊ መስተጋብሩን ያለገደብ እንዲያካሂድ እና ልማት እንዲፋጠን ነው ብለዋል።
ሕዝቡም ይህንን በውል መገንዘብ እና ጽንፈኛውን ቡድን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ሰላሙን ሊያረጋግጥ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል። መንግሥት ሕግን ለማስከበር እና ሕዝብን ከእንግልት ለማላቀቅ ቁርጠኛ መኾኑንም ተናግረዋል። አቶ ይርጋ “ሕዝቡ በስሙ እየማሉ የሚገድሉትን ጽንፈኞች ደፍሮ ‘ተው’ ማለት፤ ለሱ ብለው የሚሞቱለትን የጸጥታ አካላት መተባበር አለበት” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ሕዝቡ ሁለት አማራጭ ነው ያለው ያሉት ኀላፊው የመጀመሪያው እና ጠቃሚው አማራጭ ለሱ ሲሉ ከሚሞቱለት የጸጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ ሰላሙን ማስፈን እና በሙሉ አቅሙ ማልማት ነው ብለዋል። ሁለተኛው እና የብልሆች ያልኾነው አማራጭ ደግሞ በስሙ እየማሉ የሚቀሙትን እና የሚገድሉትን ጽንፈኞች በመፍራት እና ዝም በማለት በስቃይ እና በእንግልት ውስጥ መኖር ነው ብለዋል።
ሁለተኛው አማራጭ ሀገርን ወደኋላ የሚጎትት እና ለሕዝብ እቆረቆራለሁ የሚል መንግሥትም ሊታገሰው የማይችል አካሄድ መኾኑን ጠቁመዋል። የመንግሥት ፍላጎት ያለአንዳች ግጭት እና መስዋዕትነት ሰላም እና ልማትን ማስፈን ነው ብለዋል። ለአጥፊዎች ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ መቅረቡም የዚሁ ማሳያ ስለመኾኑ ጠቅሰዋል።
ሰላምን የማይቀበሉ የጽንፈኛው ቡድን አባላትን ለማረም የሚደረገው የሕግ ማስከበር ሥራ ይቀጥላል፤ ሕዝቡ ራሱን ከአልባሌ ድርጊቶች ቆጥቦ ይልቁንም መረጃ በመስጠት ተባባሪ መኾን አለበት ሲሉም አሳስበዋል አቶ ይርጋ።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን