በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየተሠሩ የሚገኙ የጥናት እና ምርምር ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተጠቆመ።

25

ጎንደር: ሚያዝያ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 31ኛ ዙር የጥናት እና ምርምር ጉባኤ እየተካሄደ ነው። ዩኒቨርሲቲው እያከበረ ከሚገኘው 70ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉ ጋር በማያያዝ ነው የምርምር ጉባኤውን ተመራማሪዎች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት እያካሄደ የሚገኘው።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሥራት አፀደወይን (ዶ.ር) ባለፉት ጊዜያት በተለያዩ ምክንያቶች ጉባኤው ሳይካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል። የዚህ ዓመቱ ጉባኤ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ተመራማሪዎች የተሳተፉበት መኾኑን ነው የጠቆሙት።

እንደ ዶክተር አሥራት ገለጻ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዘርፎች ያከናወናቸው የጥናት እና ምርምር ሥራዎች የማኅበረሰቡን ችግሮች ከመፍታት ባለፈ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በዩኒቨርሲቲው ከ1 ሺህ በላይ ምርምሮች በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ተመዝግበዋል።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመቀጠል ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመኾን እየሠራ እንደሚገኝ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ራስ ገዝ ለመኾን ከመሥራት በተጨማሪ ተቋማቸው ችግር ፈቺ የጥናት እና ምርምር ሥራዎችን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ.ር) በበኩላቸው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ዓመታት በርካታ የምርምር ሥራዎች ላይ ሲሳተፍ እንደነበር አንስተዋል። እንደ ሀገር የተጀመሩ የኢኮኖሚ ለውጦችን ለማስቀጠል የምርምር ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም ዶክተር ሳሙኤል ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኛው በበኩላቸው ከተማ አሥተዳደሩ እና ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዘርፎች በጋራ እየሠሩ መኾናቸውን አስታውቀዋል።

በተለይም ደግሞ የትምህርት ዘርፉን እና የጤናውን ዘርፍ በሚገባ እየደገፈ እንደሚገኙ ያስታወቁት ከንቲባው የተጀመሩ ድጋፎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እና ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ከምርምር ጉባኤው ጎን ለጎን በዩኒቨርሲቲው የተሠሩ የፈጠራ ውጤቶች ኢግዚቢሽን እየተካሄደ ይገኛል።

በጉባኤው ተመራማሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ናቸው።

ዘጋቢ፦ ደስታ ካሳ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የጋሸና- ላሊበላ- ብልባላ- ሰቆጣ አስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ቀሪ ሥራዎች ማጠናቀቂያ ሥራን አስጀመሩ።
Next article“በሕዝብ ጥያቄ ሰበብ ሕዝብን መበደል ሊቆም ይገባል” አቶ ይርጋ ሲሳይ