
ደብረ ማርቆስ: ሚያዚያ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ አዘጋጅነት “ከፈተና ወደ ልዕልና” በሚል መሪ መልዕክት በትምህርት ዘርፉ ላይ እየደረሰ ያለውን ተጽዕኖ እና የቀጣይ መፍትሔዎች ዙሪያ የሚመክር ውይይት በደብረ ማርቆስ ከተማ ተካሂዷል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኅላፊ ጌታሁን ፈንቴ በ2017 የትምህርት ዘመን ከ713 ሺህ 610 የቅድመ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ ማሳካት የተቻለው 12 ነጥብ 7 በመቶውን ብቻ መኾኑን ገልጸዋል።
እንደ ክልል በተከሰተው የጸጥታ ችግር ከ622 ሺህ 761 በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል ብለዋል። ከ622 በላይ የሚኾኑ የትምህርት ተቋማት ላይ ጉዳት ደርሷል ነው ያሉት። በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት በጋራ መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር በትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ለመውጣት ችግሮችን ለይተን በቀጣይ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲጀመር እና ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ የሚመለሱበትን ዕድል መፍጠር የሚያስችል መፍትሄ ማስቀመጥ ይገባል ብለዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ እና የውኃ ሃብት ልማት ጉዳይ ቋሚ ኮምቴ ሰብሳቢ ከፋለ ሙላቴ አሁን ላይ በትምህርት ዘርፉ ላይ የደረሰውን ችግር ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም ማኅበረሰቡን በማሳተፍ እና የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ እና መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ ለማስጀመር እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡
በንቅናቄ መድረኩ የትምህርት ባለድርሻ አካላት እና ሌሎች የሚመለከታቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን