የኮሌራ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በትኩረት እየሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞኑ ጤና መምሪያ ገለጸ።

19

ፍኖተ ሰላም: ሚያዝያ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኮሌራ አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት በማስከትል በሰውነት ውስጥ የሚገኝን ፈሳሽ አሟጦ በማስወጣት እና አቅምን በማዳከም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው።

ወረርሽኙን አስመልክቶ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት በምዕራብ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ የጤና መረጃ ጥንቅር እና ትንተና ባለሙያ ሽታሁን ጌታሁን በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን ተናግረዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በቡሬ ከተማ አሥተዳደር ባጉና ከበሳ ቀበሌ መከሰቱን ነው የገለጹት። በዞኑ 127 ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸውንም ተናግረዋል።

ወረርሽኙ በተከሰተበት ቦታ ድጋሚ እንዳይከሰት እና ስርጭቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋ ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመተባበር ጸበል ቦታዎች ላይ የግል እና የአካባቢ ንጽህና መጠበቅ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል ።

የኮሌራ ወረርሽኝ በዋናነት የሚያሳያቸው ምልክቶች ያለማቋረጥ ተቅማጥ እና ትውኪያ ስለኾነ እነዚህን ምልክቶች ማኅበረሰቡ ሲያጋጥሙት በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ህክምና ማግኘት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል ።

በዞኑ አጣዳፊ የኾነው የኮሌራ ወረርሽኝ በሌሎች አካባቢዎች እንዳይከሰት ማኅበረሰቡ የግል እና የአካባቢውን ንጽህና በመጠበቅ የበኩሉን እንዲወጣ አቶ ሽታሁን ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየመንግሥት ሠራተኛው ሰላምን ለማጽናት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ኅላፊነት ሊወጣ ይገባል።
Next articleየፈተና ጥሪ ማስታወቂያ