
ጎንደር: ሚያዝያ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ዙሪያ በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከሚገኙ የነጋዴው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት ተካሂዷል። ውይይቱ በጎንደር ከተማ በሚገኙ ስድስት ክፍለ ከተሞች ከሚገኙ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ጋር እየተደረገ ነው።
በውይይቱም ”የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክት በክልሉ እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችን የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ቀርቧል። የውይይቱ መደረግ በክልሉ እየደረሱ ባሉ ውድመቶች ዙሪያ የነጋዴው ማኅበረሰብ ግንዛቤ እንዲኖረው ያለመ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ተናግረዋል።
በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ሕዝቡን ለበርካታ ውስብስብ ችግሮች ዳርጎታል ብለዋል። ባለፉት ዓመታት የተዘራው የአስተሣሠብ ዝንፈት አሁን ላለንበት ምስቅልቅል እንድንገባ አድርጎናል ያሉት ከንቲባው በከተማ አሥተዳደሩ በትምህርት ገበታ መገኘት የነበረባቸው ከ26 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ርቀዋል ብለዋል።
አሁንም የልማት ሥራዎች በጸጥታ ኃይሎች ታጅበው እየተሠሩ መኾኑን ገልጸው አሁን ያገኘናቸውን የልማት እድሎች በአግባቡ ለመጠቀም ሁሉም ሊያግዝ ይገባል ነው ያሉት። የነጋዴው ማኅበረሰብ በሰላም እጦቱ ምክንያት ችግር ውስጥ መግባቱን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አንስተዋል። በጋራ መቆም አሁን ካለንበት ችግር እንድንወጣ የሚያግዝ በመኾኑ ማኅበረሰቡ እና ነጋዴው የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
መላ ኢትዮጵያውያን ለጎንደር ልማት መረባረባቸውን የገለጹት አቶ ቻላቸው የንግዱ ማኅበረሰብ እና ነዋሪዎች ለከተማዋ ልማት መፋጠን አበርክቶ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። በውይይቱ ተሳታፊ የኾኑ የነጋዴው ማኅበረሰብ አባላት በሰላም እጦቱ ሳቢያ ለነዋሪዎች አስፈላጊ የኾኑ ግብዓት በወቅቱ ባለመድረሳቸው የኑሮ ውድነቱ እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል።
ሰላምን ለማምጣት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ:- ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን