
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) በጂቡቲ ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ 117 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ፡፡ ይህንን ተከትሎም አጠቃላይ በሀገሪቱ በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ወደ 1 ሺህ 518 ማሻቀቡን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ዛሬ ማለዳውን አስታውቋል፡፡
የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር በመግለጫው እንዳስታወቀው ለ813 ሰዎች የናሙና ምርመራ ተደርጎ ነው በ117 ሰዎች ላይ ቫይረሱ የተገኘው፡፡ በ24 ሰዓታት ውስጥ 46 ሕሙማን ማገገማቸውን ያስታወቀው ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ አጠቃላይ 1 ሺህ 18 ሰዎች ከቫይረሱ ማገገማቸውንም አመላክቷል፡፡
በአጠቃላይ በጂቡቲ ለ18 ሺህ 345 ሰዎች ምርመራ ተደርጓል፡፡ ሰባት ሰዎች ደግሞ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ጂቡቲ ቀይ ባሕርን ከኤደን ባሕረ ሰላጤ የምታገናኝ ቁልፍ ሀገር ስትሆን በርካታ የውጪ ሀገራት የጦር ካምፕ መገኛ መሆኗንም ሲ ጂ ቲ ኤን በዘገባው አስታውሷል፡፡
ሀገሪቱ የኢትዮጵያ ዋነኛ የወጪና ገቢ የንግድ በር በመሆኗ የቫይረሱ በጂቡቲ መስፋፋት ለኢትዮጵያም ከፍተኛ ስጋት የሚደቅን ነው፡፡
በደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡