ግጭቱ የሚጎዳው እኛኑ ስለኾነ ለሰላሙም መሥራት ያለብን እኛው ነን ሲሉ የአዴት ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

23

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም ዞን የአዴት ከተማ አሥተዳደር እና የይልማ እና ዴንሳ ወረዳ ነዋሪዎች ”የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል መልዕክት የሰላም ውይይት እያካሄዱ ነው። በውይይቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው ግጭት የደረሱ ጥፋቶችን የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ቀርቧል።

ተወያዮችም ባነሱት ሃሳብ ወንድማማቾች መጠፋፋት የለባቸውም። የተማረው አካል የሚሠራው እና የሚያስተምረው ለሕዝብ እና ለሀገር መኾን አለበት። እኔን ከተመቸኝ ምን አገባኝ ማለት መቅረት አለበት ነው የተባለው። መከላከያ ሠራዊት ሰላም ለማስፈን ለከፈለው መስዋዕትነት ምሥጋና በተሰጠበት መድረክ ሕዝቡ ለውይይት መጠራቱም ተገቢ መኾኑ ተነስቷል። ሕዝቡም ዝም ባለ ቁጥር ጥፋቱ እና ውድመቱ እየጨመረበት እንደሚሄድ ተመላክቷል።

ግጭቱ ወንድም ከወንድሙ ጋር መኾኑ ደግሞ አሸናፊ የሌለበት እና መቆሚያ የሌለው ጥፋት እያስከተለ ስለኾነ መቆም አለበት ነው የተባለው። ሕዝቡም በቃ ማለት እንዳለበት ተነስቷል። ጽንፈኝነት አስቸጋሪነቱ እኔን ብቻ ስሙኝ ማለቱ ነው፤ የራሱን ወንድሞች የሚገድል ሌላውን ነጻ ሊያወጣ አይችልም፤ በጦርነት ችግር አይፈታም፤ ብሎ ብሎ በውይይት ለሚፈታ ጉዳይ አሁን ላይ ሕዝብ መጎዳት የለበትም፤ መንግሥትም አሁንም ገፍቶ ለሰላም መሥራት አለበት ተብሏል።

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ መሞከር የማይሳካ ነው፤ በአንጻሩ ግጭትን እንደመጠቀሚያ የሚፈልግም ስለሚኖር በደንብ መፈተሽ አለበት ነው የተባለው። ይልማና ዴንሳ የምርት ሀገር ነው፤ በጥባጮች በመኖራቸው ግን ሰላማችን አጥተን አሟሟታችን እየከፋ ነው ብለዋል።

አንዱ ልጄ የመከላከያ አባል ኾኖ በወሎ አለ፤ ሌላው ልጄ በጽንፈኞች ጎራ ኾኖ ለሁለት ተከፍየ ነው ያለሁት፤ እርቀ ሰላም ቢወርድልኝ መልካም ነበር ያሉ ሃሳብ ሰጭም አሉ። ግጭቱ ሲጀመር የአማራን ሕዝብ ጥቅም እና መብት አስከብራለሁ ነበር፤ የሚታየው ግን የአማራ ልጅ እንዳይማር፣ አርሶ አደሩ ማዳበሪያ እንዳያገኝ እየተከለከለ፣ እየተገደለ መኾኑ ተነስቷል። በመኾኑም ሕዝቡ አደረጃጀት ፈጥሮ ራሱን እና አካባቢውን መጠበቅ እንዳለበት ነው ከመድረኩ የተገለጸው።

ሀገር ችግር ሲገጥማት መሸሽ፣ አሉቧልተኝነት፣ ችግርን በግልጽ በድፍረት መናገር እና መታገል እንደሚገባም ተብራርቷል። የመንግሥትን ችግሮች ሀገር በሚያፈርስ መልኩ ሳይኾን በሰላማዊ መንገድ መታገል እንደሚገባም ተነስቷል። አማራ ክልል በሕወሓት ጦርነት አሁን ደግሞ በእርስ በእርስ ግጭት አደጋ ውስጥ መግባቱ እና በስክነት በማየት ለሰላም መሥራት እንደሚገባ ተወስቷል። ለዚህም ልጆቻችን መምከር አለብን ነው የተባለው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article20ኛው የሌበር ቤዝድ አሕጉር አቀፍ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው፡፡
Next article“ጎንደር ያገኘቻቸውን የልማት እድሎች በአግባቡ ለመጠቀም ሁሉም ነዋሪዎች ሊያግዙ ይገባል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው።