
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የ20ኛው የሌበር ቤዝድ አሕጉር አቀፍ ኮንፈረንስን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። ጋዜጣዊ መግለጫውን የሠጡት የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ኮንፈረንሱ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር እና ዓለም አቀፉ የላባደሮች ድርጅት (አይኤልኦ) በጋራ በመተባበር የሚያካሂዱት ነው ብለዋል።
ኮንፈረንሱ ከግንቦት 11/2017 እስከ ግንቦት 15 /2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ የገለጹት ሚኒስትሯ እንግዶችን ለመቀበል አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል። ኮንፈረንሱ “የማይበገር ማኅበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ የሠው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከበርም ገልጸዋል።
በአሕጉራዊ ኮንፈረንስ ሀገራት በሚተገብሯቸው የተለያዩ የመሠረተ ልማት እና ሌሎች ፕሮግራሞች የሰው ኃይልን በስፋት በመጠቀም፣ ዘላቂ እና ጥራት ያለው የሥራ ዕድልን በመፍጠር፣ የሠራተኞችን ዘላቂ ተጠቃሚነት እና ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ ያላቸውን ተሞክሮ የሚያካፍሉበት ነው ብለዋል ሚኒስትሯ በመግለጫቸው።
በኮንፈረንሱ ስለ ሀገራት የቴክኖሎጅ አጠቃቀም፣ የሰው ኃይል የሥራ ደኅንነት፣ ሥለ አየር ንብረት ለውጥ ውይይት ይደረጋል፤ የምርምር ውጤቶችም ይቀርባሉ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ። በተለይም ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ እና በአረንጓዴ ልማት፣ በኮሪደር ልማት፣ በመንገድ እና በሌሎች መሠረተ ልማቶች የሠራቻቸው ሥራዎች እና ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች እና ተሞክሮ ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብ የምታስተዋውቅበት ነው ብለዋል።
በአሕጉራዊ ኮንፈረንሱ 1 ሺህ 500 የተለያዩ ሀገራት ዜጎች እንደሚሳተፉም ተናግረዋል። በኮንፈረንሱ የተለያዩ ሀገራት ሚኒስትሮች፣ የዓለማቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት፣ የአሰሪዎችና ሠራተኞች ፌደሬሽኖች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች እና ባለሙያዎች፣ የፈጠራ ባለቤቶች የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ ፖሊሲ አውጭዎች ይሳተፋሉ ተብሏል።
ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን