
ደብረ ብርሃን: ሚያዝያ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የጠባሴ ክፍለ ከተማ የትምህርት መሪዎች፣ የመምህራን እና የአሥተዳደር ሠራተኞች “የጥፋት እጆች እና መዘዞቻቸው” በሚል መሪ መልዕክት ውይይት አካሂደዋል። የሰላም እጦቱ በመማር ማስተማር ሥራው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማስከተሉን በመድረኩ ላይ የተሳተፉ መምህራን ተናግረዋል።
ሰላምን ለማምጣት በሚሠራው ሥራ ኅብረተሰቡ የድረሻውን እንዲወጣም በመድረኩ ተጠይቋል። የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መቅደስ ብዙነህ በበኩላቸው በነበረው የሰላም ችግር በከተማ አሥተዳደሩ 1ሺህ 300 በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ያጋጠመው የሰላም እጦቱ በደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ ሰባት ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲያቋርጡ ማድረጉ ነው የተብራራው። የትምህርት ባለድርሻ አካላት ሰላምን ለመፍጠር በሚሠራው ሥራ የበኩላቸውን ኀላፊነት ሊወጡ እንደሚባም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮፓሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ብርሃኑ ጣዕምያለው ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በነበረው የሰላም ችግር በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና መሰል ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ተግዳሮቶች መግጠሙን ተናግረዋል።
የሰላም እጦት የትምህርት ተቋማት መደበኛ ሥራቸውን እንዳይሠሩ እክል የፈጠረ በመኾኑ የትምህርት ሥራውን ለማስቀጠል የሚያስችል ሥራ መሥራት ይጠይቃል ነው ያሉት።
መምህራን እና ባለድርሻ አካላት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ሰላምን ለማምጣት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ፋንታነሽ መሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን