የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል የተመለመሉ ወጣቶች ሽኝት ተደረገላቸው።

35

ደብረ ማርቆስ: ሚያዝያ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል የተመለመሉ ወጣቶች ወደ ሥልጠና ማዕከል ሽኝት ተደርጎላቸዋል።

ወጣቶቹ ክቡር የኾነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመቀላቀላቸው ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል። ሥልጠናቸውን በብቃት በመውሰድ ሕዝባቸውን እና ሀገራቸውን በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋየ በላይ ሀገር እና ሕዝብን ለማገልገል ወደ ትልቁ ሀገራዊ ተቋም በመቀላቀላችሁ ትልቅ ክብር ይገባችኋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በየዘመኑ የሚገጥሟትን የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎች በልጆቿ ኅብረት እየመከተች ዛሬ እዚህ ላይ ደርሳለች ነው ያሉት።

ኀላፊው ወጣቶቹን ሀገርን በላብ እና በደም አጽንቶ በኅብረ ብሔራዊነት ዕድገቷን ለማስቀጠል ውስጣዊ አቅምን ለማሳደግ ትልቅ ኀላፊነት ተጥሎባችኋል ብለዋል።

በተሰለፋችሁበት መስክ ሀገራችሁን በታማኝነት በማገልገል የዜግነት ድርሻችሁን መወጣት አለባችሁም ነው ያሉት።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያን የሚገልጽ ትልቁ ሀገራዊ ተቋም መኾኑን የተገነዘበ ወጣት እየተፈጠረ መምጣቱን የተናገሩት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አበባው በለጠ ናቸው። ኀላፊው ከእርስ በእርስ ግጭት በመውጣት ሀገራዊ አንድነትን ለማናጋት የሚጥሩ ኀይሎችን ለመታገል ጠንካራ የሀገር መከላከያ ተቋም ለመገንባት መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleከፍተኛ መሪዎች ከጎንደር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ ያለመ ጉብኝት እያደረጉ ነው።