የኮሌራ በሽታ አሁንም ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ነው።

28

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኮሌራ በባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰት በሽታ ነው። በሽታው ሲከሰት አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት በማስከተል የሰውነትን ፈሳሽ አሟጦ እንዲወጣ የሚያደርግ አደገኛ በሽታ ነው። አፋጣኝ ሕክምና ካልተደረገለት ደግሞ አቅምን በማዳከም በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡

የተበከለ ውኃ፣ የተበከለ ምግብ መመገብ፣ በግል እና በአካባቢ ንጽህና ጉድለት፣ ሜዳ ላይ መጸዳዳት፣ የመጸዳጃ ቤቶችን በአግባቡ አለመጠቀም ወዘተ ዋና ዋና መተላለፊያ መንገዶች ናቸው። በበሽታ አምጭ ተህዋስያን የተበከለ የምንጭ፣ የወንዝ፣ የዝናብ፣ የቧንቧ እና የሐይቅ ውኃን መጠቀም፣ በበሽታ አምጭ ተህዋስያን የተበከለ የውኃ ማጠራቀሚያ እና መገልገያ እቃዎችን በአግባቡ ሳያጸዱ መጠቀም፣ እጅን ሳይታጠቡ ምግብን ማዘጋጀት እና መመገብም የበሽታው መተላለፊያ ተደርገው ይወሰዳሉ።

በበሽታው አምጪ ተህዋስያን የተበከለ ምግብ፣ አትክልቶችን እና ፍራፍሬዎችን መመገብ፣ ክዳን የሌላቸውን እና ለዝንቦች የተጋለጡ የምግብ ማስቀመጫ እና መመገቢያ እቃዎችን መጠቀም፣ የኮሌራ ታማሚ ተቅማጥ እና ትውከት በአግባቡ አለማስወገድ፣ ከኮሌራ ታማሚ ጋር ንክኪ የነበራቸው ቁሳቁሶች እና ተሸከርካሪዎችን በአግባቡ ሳይጸዱ መልሶ መጠቀም ሌሎች መተላለፊ መንገዶች ናቸው።

በድንገት የሚከሰት ብዛት ያለው አጣዳፊ ውኃ መሰል ተቅማጥ እና በተደጋጋሚ ማስመለስ የበሽታው ምልክቶች ናቸው። ቶሎ ሕክምና ካልተገኘ በሰውነት ያለው ፈሳሽ ተሟጥጦ ስለሚያልቅ የአቅም ማነስ፣ የቆዳ መሸብሸብ ፣ የዐይን መሰርጎድ፣ የአፍ መድረቅ አለፍ ሲልም ሞት ያስከትላል።
👉 በአማራ ክልል የበሽታው አሁናዊ ሁኔታ ምን መልክ አለው?

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ማሥተባበሪያ ማዕከል ቡድን መሪ አሞኘ በላይ የኮሌራ በሽታ በክልሉ በተለያዩ ዓመታት ተከስቶ ጉዳት አድርሷል ብለዋል። በዚህ ዓመትም ከታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 18/2017 ዓ.ም ድረስ በተከሰተው በሽታ 2 ሺህ 115 ሕሙማን ሪፖርት ተደርጓል ነው ያሉት።

አሁን ላይ በምዕራብ ጎንደር ዞን በቋራ ወረዳ፣ በሰሜን ጎጃም ዞን፣ ባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ፣ በባሕር ዳር ከተማ፣ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጃዊ ወረዳ እና በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ከተማ በሽታው መኖሩን ተናግረዋል።

በሽታውን ለመቆጣጠር ክስተቱ ባለባቸው ቦታዎች ላይ ጊዜያዊ የሕክምና ጣቢያዎች ተቋቁመዋል ብለዋል። የታመሙትም ተለይተው ሕክምና እየተሰጣቸው መኾኑን ነው የተናገሩት። ለበሽታው ተጋላጭ በኾኑ አካባቢዎች የግንዛቤ ፈጠራ እና ብክለትን የመከላከል ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

👉 በሽታውን ለመከላከልም በማኅበረሰቡ መደረግ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች ተቀምጠዋል!

የመጀመሪያው መከላከያ መንገድ መጸዳጃ ቤቶችን በአግባቡ መጠቀም ነው። መጸዳጃ ቤቶችን በአግባቡ መጠቀም ከኮሌራ ሕሙማን የሚወጣውን ተቅማጥ እና ትውከት አካባቢን እና ውኃማ አካላትን ከብክለት ይከላከላል።

ሌላው ንጹህ ውኃ መጠቀም ትልቁ መፍትሔ ነው። የንጹህ መጠጥ ውኃ በሌለበት አካባቢ ደግሞ ውኃን አፍልቶ እና አቀዝቅዞ መጠጣት ወይም በውኃ ማከሚያ ኬሚካል አክሞ መጠቀም በሽታውን ለመከላከል አይነተኛ መፍትሔ ነው። የውኃ ማጠራቀሚያ እቃዎችን ሁልጊዜ በታከመ ወይም በፈላ ውኃ ማጠብ እና መክደን ይገባል።

የምግብ ንጽሕናን መጠበቅ፣ ምግብን በሚገባ አብስሎ ከተቻለ በትኩስነቱ መመገብ ሌላው መከላከያ መንገድ ነው። ንጹህ የማብሰያ ዕቃዎች እና ሳህኖችን መጠቀም፣ ለምግብነት የተዘጋጁ ምግቦችን ካልተዘጋጁ ምግቦች ለይቶ ማስቀመጥ፣ ከመጸዳጃ ቤት መልስ፣ ምግብ ከማዘጋጀት እና ከመመገብ በፊት እንዲሁም ለኮሌራ ሕሙማን እንክብካቤ ከተደረገ በኋላ እጅን በንጹህ ውኃ እና ሳሙና መታጠብ ይገባል።

ከቤት የሚወጡ ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻዎች አካባቢን እና ውኃን እንዳይበክሉ በአግባቡ ማስወገድም ሌላው መፍትሔ ነው። ከምልክቶቹ አንዱ በታየ ጊዜ ወደ ሕክምና ተቋም እስኪደረስ ድረስ ቤት ውስጥ በሚገኝ ማንኛውንም ንጽህናውን የጠበቀ ፈሳሸ መውሰድ ያስፈልጋል።

ሕክምና እስኪ ደርሱ ከሰውነት የሚወጣውን ፈሳሽ ለመተካት በቤት ውስጥ ካለ አንድ ፓኬት ሕይወት አድን ንጥረ ነገር ወይንም”ኦ አር ኤስ” ፈልቶ በቀዘቀዘ አንድ ሊትር ውኃ በመበጥበጥ መጠጣት ያስፈልጋል።

“ኦ አር ኤስ” ከሌለ ደግሞ ስድስት የሻይ ማንኪያ ስኳር እና ግማሽ የሻይ ማንኪያ ጨውን በአንድ ሊትር ንጹሕ ውኃ በጥብጦ መጠጣት ያስፈልጋል። ኦ አር ኤስን መጠቀም የሚቻለው በተበጠበጠ በ24 ሰዓት ውስጥ ብቻ ነው። ጡት የሚጠቡ ህጻናት በበሽታው ከተያዙ ደግሞ ከተለመደው በመጨመር ጡት ማጥባት ይገባል ነው ያሉት ቡድን መሪው።

ቡድን መሪው እንዳሉት ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር ተቋማት ተቀናጅተው ሊሠሩ ይገባል። ጤና ቢሮ ባለሙያዎችን በማሠልጠን ሕሙማንን የማከም፣ መጸዳጃ ቤት የመገንባት፣ ለማኅበረሰቡ ደግሞ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ አየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ውኃ ቢሮ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የሃይማኖት አባቶች ደግሞ ችግሩ በተከሰተባቸው የጸበል ቦታዎች በጊዜያዊነት አገልግሎቱን ማቋረጥ እንዳለባቸው አንስተዋል።

ስለወረርሽኙ አስከፊነት እና አሳሳቢነትም ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ሊፈጥሩ ይገባል ብለዋል።

የጉዞ ማኅበራት ኀላፊነት እንዲወስዱ፣ የትራንስፖርት ዘርፉ ደግሞ ለማኅበረሰቡ ጤና ጠንቅ የሚኾኑ እንቅስቃሴዎችን ሊያስቆም ይገባል ብለዋል።

ማኅበረሰቡም የጤና ባለሙያዎች የሚሠጡትን ትምህርት፣ በመንግሥት እና በሃይማኖት አባቶች የሚተላለፉ መልዕክቶችን እንዲተገብር አሳስበዋል።

የበሽታው ምልክት ከታየ ደግሞ ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋማት በመሔድ ሕክምና ማግኘት ይገባል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበሰሜን ጎጃም ዞን ከአዴት ከተማ አሥተዳደር እና ይልማና ዴንሳ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ሕዝባዊ የሰላም ውይይት እየተካሄደ ነው።
Next articleከፍተኛ መሪዎች ከጎንደር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።