“የተሠሩ የምርምር ሥራዎች በሰፊው ተመርተው ወደ ገበያ መቀላቀል አለባቸው” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)

45

ደሴ: ሚያዝያ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ያዘጋጀው ዘጠነኛው የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ፣ የጥናት እና ምርምር እንዲኹም የኢንተርፕራይዞች ሽግግር ባዛር እና አውደ ርዕይ ተጠናቅቋል።

በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)፣ የክልሉ ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) እና ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ከሚያዝያ 18/2017 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 23 የቆየው መርሐ ግብሩ የፈጠራ ሥራን ማበረታታት፣ የሥልጠና ጥራትን ማረጋጋጥ፣ ቴክኖሎጂን መቅዳት እና ማሸጋገር እንዲኹም ልማታዊ ባለ ሀብት ማፍራትን ያነገበ መኾኑን የክልሉ ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ምክትል ኀላፊ እና የትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ አሥተባባሪ አማረ ዓለሙ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው(ዶ.ር) በዝግጅቱ የቀረቡ የፈጠራ ሥራዎች በተለይ የግብርናውን ዘርፍ ከማዘመን አንጻር ከፍተኛ ሚና ያላቸው መኾኑን አንስተዋል። የአርሶ አደሮችን የምርት ጥራት የሚጠብቁ፣ ብክነትን የሚያስቀሩ እና ጊዜ እና ጉልበትን የሚቆጥቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የፈጠራ ሥራዎቹ ተኪ ምርት ኾነው በማገልገል እና የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረት አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው መኾኑንም ተናግረዋል።

አኹን የታዩ የፈጠራ ሥራ ውጤቶች እና ምርምሮች በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚደረገው ውድድር ለአሸናፊነት የሚያበቁ ስለመኾናቸውም ቢሮ ኀላፊው አንስተዋል። የክልሉን የፈጠራ አቅም ለመጨመር እና መሰል ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የክልሉ ሥራና ሥልጠና ቢሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የከተማ ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) “ያየናቸው የምርምር እና የቴክኖሎጂ ዘርፍ የፈጠራ ሥራዎች የሀገራችንን የማደግ እና የመበልጸግ ተስፋ አመላካቾች ናቸው” ብለዋል። የግብርናውን ዘርፍ የሚያዘምኑ የፈጠራ ውጤቶችን መመልከታቸውን ገልጸዋል። ይህም ለሀገሪቱ መለወጥ ጉልህ ሚና ያለው መኾኑን ተናግረዋል። ሀሳብን ወደ ተግባር በመቀየር ለሕዝብ ተጠቃሚነት መሥራት እንደሚገባም ነው ያነሱት።

ሀሳብን ወደ ፈጠራ ለመቀየር ደፋ ቀና የምትሉ አካላትም በርትታችሁ ልትሠሩ ይገባል፤ መንግሥትም ተገቢውን ማበረታቻ ያደርጋል” ነው ያሉት። “የተሠሩ የምርምር ሥራዎች በሰፊው ተመርተው ወደ ገበያ መቀላቀል እንዳለባቸውም” አሳስበዋል። በጋራ በመሥራት የፈጠራ ሥነ ምህዳርን ማስፋት እንደሚገባም ነው ያመላከቱት። ዘርፉን ለማዘመን ተቋማት በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባም ነው አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) የገለጹት።

በዚህ መርሐ ግብር የታዩ የፈጠራ ሥራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ውድድር በቂ ዝግጅት ማድረግ እና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ሳይታክቱ መሥራት እንደሚገባም ነው አደራ ያሉት። በኮምቦልቻ ከተማ ለተካሄደው መርሐ ግብር ስኬታማነት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋናም አቅርዋል።

ዘጋቢ: አሊ ይመር

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአሲዳማ አፈር የግብርናው ዘርፍ ፈተና ኾኗል።
Next articleበሰሜን ጎጃም ዞን ከአዴት ከተማ አሥተዳደር እና ይልማና ዴንሳ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ሕዝባዊ የሰላም ውይይት እየተካሄደ ነው።