የአሲዳማ አፈር የግብርናው ዘርፍ ፈተና ኾኗል።

13

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አሁን ላይ 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በመኸር፣ 342 ሺህ 480 ሄክታር መሬት በመስኖ፣ 239 ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ በበልግ መልማት የሚችል መሬት አለው። ክልሉ አጠቃላይ በሀገሪቱ ከሚለማው መሬት 34 በመቶ፣ በምርት ደግሞ 36 በመቶ ድርሻ እንዳለው የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል።

ክልሉ ከሀገሪቱ ከሚለማው መሬት እና ከሚመረተው ምርት ከፍተኛ ድርሻ ቢኖረውም አጠቃላይ የክልሉ የቆዳ ስፋት ይኾናል ተብሎ ከሚገመተው ከ19 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ ከ5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በአሲዳማነት የተጠቃ ነው። የአሲዳማነት ችግሩ ጎልቶ ከሚታይባቸው አካባቢዎች ውስጥ ደግሞ አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አንዱ ነው።

የአፈር አሲዳማነት ችግር ምን ያህል ፈታኝ እንደኾነ፣ ከታከመ ደግሞ ምርታማነቱ እንደሚሻሻል በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባንጃ ወረዳ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር ደሳለው በላቸው ነግረውናል። አርሶ አደር ደሳለኝ የአፈር አሲዳማነት በግብርናው ዘርፍ በተለይም ደግሞ በሰብል ምርት ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ብለዋል።

አርሶ አደር ደሳለኝ የሚያለሙት 3 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ለብዙ ዘመን በመታረሱ ምርታማነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደቀነሰባቸው ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ አንድ ሄክታር ተኩል የእርሻ መሬታቸው በአሲዳማነት በመጠቃቱ ምርት መስጠት አቁሞ ነበር። በግብርና የአፈር ናሙና ተወስዶ በአሲዳማነት መጠቃቱ በመረጋገጡ ባለፉት ዓመታት በኖራ እንዲታከም ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ከኖራ በተጨማሪ የተፈጥሮ ማዳበሪ ጭምር አቀናጅተው በመጠቀማቸው በፊት ይገኝ ከነበረው ምርት ከሦስት እጥፍ በላይ ጭማሪ ማሳየቱንም ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ በስንዴ ምርት ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ነው የተናገሩት። አሁን ላይ ደግሞ ወደ ግማሽ ሄክታር መሬት የሚጠጋ በአሲዳማ አፈር የተጠቃ መሬት ለማከም እንዳቀዱም ነግረውናል። ኖራ ምርታማነትን የመጨመር አቅሙ ከፍተኛ መኾኑን ያነሱት አርሶ አደሩ በአቅርቦት ምክንያት የተጎዳውን መሬት በሙሉ ማከም አለመቻላቸውን ነው የነገሩን።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ አንዱዓለም አያሌው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሊታረስ ከሚችለው 406 ሺህ 246 ሄክታር መሬት ውስጥ 46 በመቶው በአሲዳማ አፈር የተጠቃ ነው ብለዋል። ችግሩን ለመከላከል በየዓመቱ እስከ 500 ሄክታር በአሲዳማ አፈር የተጠቃ መሬት በኖራ እና በተፈጥሮ ማዳበሪያ ጭምር የማከም ሥራ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት። የአፈር እና ጥበቃ ሥራ፣ ተራራማ እና ተዳፋታማ ቦታዎችን ደግሞ የችግኝ ተከላ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

በዚህም ማብቀል የማይችሉ መሬቶች ምርት እንዲሠጡ ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል። ምርታማነታቸው የቀነሱትን ደግሞ እስከ ሦስት እጥፍ ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት። በዚህ ዓመትም 1ሺህ 629 ሄክታር የሚጠጋ መሬት ለማከም ተለይቷል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ 48 ሺህ 856 ኩንታል ኖራ ለመጠቀም ተለይቶ በዝግጅት ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

በአሲዳማነት የተጠቃውን መሬት ለማከም በቂ ኖራ በመንግሥት እንዲቀርብም ጠይቀዋል። አሲዳማነት በበዛባቸው እና የኖራ ጥሬ ሀብት ባለባቸው አካባቢዎች የኖራ መፍጫ ፋብሪካዎችን ጭምር ማቋቋም አማራጭ የሌለው መፍትሔ መኾኑንም ገልጸዋል። በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ባለሙያ አጠቃ አይቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚታረሰው መሬት ውስጥ 45 በመቶው ለአፈር አሲዳማነት የተጋለጠ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል የቆዳ ስፋት ይኾናል ተብሎ ከሚገመተው 19 ሚሊዮን 470 ሺህ 896 ሄክታር መሬት ውስጥ ደግሞ 5 ሚሊዮን 537 ሺህ 451 ሄክታር መሬት አሲዳማነት ያለው እንደኾነ ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥ 601 ሺህ 607 ሄክታሩ ከፍተኛ፣ 1 ሚሊዮን 296 ሺህ 956 ሄክታሩ መካከለኛ፣ 3 ሚሊዮን 638 ሺህ 888 ሄክታሩ ደግሞ በዝቅተኛ ደረጃ አሲዳማነት የተጠቃ እንደኾነ ገልጸዋል።

በክልሉ የአፈር አሲዳማነት ችግሩ ጎልቶ የሚታይባቸው አምራች የሚባለው ምዕራቡ የክልሉ ክፍል እንደኾነ ገልጸዋል። ምዕራብ ጎጃም እና አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከፍተኛ አሲዳማነትን በመያዝ ቀዳሚውን ደረጃ ይይዛሉ። ምሥራቅ ጎጃም እና ደቡብ ጎንደር ደግሞ በሁለተኛ ጀረጃ ተቀምጠዋል ነው ያሉት። ሰሜን ጎጃም፣ ማዕከላዊ ጎንደር እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ ተቀምጠዋል ብለዋል። ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች ደግሞ አራተኛ ደረጃ ተቀምጠዋል ነው ያሉት።

በከፍተኛ ዝናብ የአፈር መከላት፣ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ፣ ተመሳሳይ ሰብል ለዓመታት ማምረት የአሲዳማነት ችግሩ እንዲባባስ ከሚያደርጉ ነገሮች ውስጥ ይጠቀሳሉ ብለዋል ባለሙያው። አሲዳማነትን ለመከላከል ሰብልን በፈረቃ መዝራት አንዱ ነው። ኖራ መጠቀም የመጀመሪያው አማራጭ ሲኾን ኖራን ከተፈጥሮ ማዳበሪያ ጋር አቀናጅቶ መጠቀም ደግሞ ፍቱን መድኃኒት ተደርጎ ይወሰዳል ነው ያሉት።

በዚህ ዓመት 12 ሺህ 360 ሄክታር መሬት ለማከም ታቅዷል። ለዚህ ደግሞ 370 ሺህ 800 ኩንታል ኖራ ለመጠቀም ታቅዷል ብለዋል። እስከ አሁን 86 ሺህ 114 ኩንታል ቀርቧል ነው ያሉት። ከቀረበው ውስጥ ደግሞ 50 ሺህ 496 ኩንታል ተሠራጭቷል፤ 14 ሺህ 524 ኩንታሉ ደግሞ ጥቅም ላይ ውሏል ብለዋል።

ይሁን እንጅ በጨረታ መጓተት ምክንያት አቅርቦቱ ዝቅተኛ መኾኑን ነው የገለጹት። ከግንቦት መጀመሪያ ጀምሮ የተሻለ ሥርጭት እንደሚኖርም ተስፍቸውን ገልጸዋል። በክልሉ ከፍተኛ የኖራ ጥሬ ዕቃ ክምችት ቢኖርም የኖራ መፍጫ ፋብሪካዎችን በማቋቋም በስፋት የማቅረብ ችግር መኖሩን ነው የተናገሩት። እስከ አሁን ከክልሉ ውጭ ምርቱን በማስመጣት ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይ ደጀን ላይ የሚገኘውን ፋብሪካ የማምረት አቅም ከማሳደግ ባለፈ ሁለተኛውን የኖራ ወፍጮ ለመትከል የሸድ ግንባታ ተጠናቋል ብለዋል። ማሽኑን ለማስገባትም እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት። በመጭው ዓመት ደግሞ በመርሐ ቤቴ ከተማ የሚገኘውን ማሽን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። ለሌሎች ሁለት ተጨማሪ የኖራ ወፍጮዎች የግዥ ጥያቄ መቅረቡንም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleአሠሪ ተቋማት ለጸደቁ ደንቦች እና መመሪያዎች ዕውቅና በመስጠት ገቢራዊ ማድረግ አለባቸው።
Next article“የተሠሩ የምርምር ሥራዎች በሰፊው ተመርተው ወደ ገበያ መቀላቀል አለባቸው” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)