“ፈጠራ እና ፍጥነት የታከለበት የክህሎት ግንባታ ቀጣይነት ላለው የሥራ እድል ፈጠራ ወሳኝ ነው” የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

30

ባሕር ዳር: ሚያዚያ: 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት እንኳን ለዓለም የሠራተኞች ቀን በሰላም አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

ሀገራችን “በአምራች ኢንዱስትሪዎች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ምቹ የሥራ ሁኔታ ለማኅበራዊ ፍትህ” በሚል መሪ ሃሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ136ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም አቀፍ ሠራተኞች በዓል እያከበረች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ የዓለም የሠራተኞች ቀንን የምታከብረው የኢንዱስትሪ ሰላምን፣ የሥራ ላይ ደኅንነትን እና የሠራተኞችን ክሕሎት ማሳደግን ልዩ ትኩረት በመስጠት ነው፡፡ ወደ ብልጽግና የሚደረገዉ ጉዞ ያለ ኢንዱስትሪ ሰላም፣ ያለ ሠራተኞች የሥራ ላይ ደኅንነት እና ዘመኑ የሚጠይቀዉን ክሕሎት ለሠራተኛዉ ሳያስታጥቁ የሚታሰብ አይደለም፡፡ በመኾኑም በዓሉን ስናከብር ሠራተኞች፣ የሠራተኛ ማኅበራት እና የክህሎት ሥልጠና ተቋማት ለኢንዱስትሪ እና ሀገራዊ ሰላም እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ ዕውቅና በመስጠት፣ አሠሪዎች ደግሞ ለሠራተኞች የሚፈጥሩትን ምቹ የሥራ አካባቢ እና የሥራ ላይ ደኅንነት በማበረታታት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለሁለንተናዊ ብልጽግና ለምታደርገዉ ጉዞ በምሰሶነት የተለዩት የምጣኔ ሃብት ዘርፎች ማለትም ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ዲጂታል ኢኮኖሚ የሠራተኞችን ሁለንተናዊ ክህሎትንና ጥረት የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግም መንግሥት ኢንዱስትሪዎች በብዛት የሚፈልጓቸዉን በመካከለኛ ደረጃ የሠለጠኑ ሠራተኞች ለማቅረብ ሰፋፊ የክሕሎት ሥልጠናዎችን በቴክኒክና ሙያ ተቋማት እና በተለያዩ አማራጮች እያቀረበ ይገኛል፡፡ የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ለዚህ አንዱ አብነት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ መርሐ ግብሩ ሠራተኞች ለአሁኑ እና ለቀጣዩ ዲጂታላይዝድ ዓለም ብቁ የሚያደርጋቸውን አቅም የሚገነባ ሲሆን ከዓለም እውቅ የኦንላይን ሥልጠና ማዕከል በነጻ የሚሰጡ አራት የሥልጠና መስኮችን የሚያካትት ነው።

የሥራ ፈጠራን እና ለሥራ ፈጠራ ምቹ የሆነ ምህዳር መፍጠር የመንግስት ዋነኛ ትኩረቶች መካከል ሲሆን ከዚህ አንጻር በዚህ ዓመት በሁሉም የኢኮኖሚ መስኮች ከሦስት ሚሊዮን በላይ ስራዎች ተፈጥረዋል። ዜጎች መብታቸው ተጠብቆ በውጭ ሃገራት ሥራዎች እንዲሰማሩ ለማድረግ መንግስት ከመዳረሻ ሃገራት መንግስታት ጋር በደረሰው ስምምነት መሰረት ከ340ሺህ በላይ የውጭ ሃገር የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ቴክኖሎጂ የፈጠረውን አስቻይነት ሚና በማስፋት ከ45ሺህ በላይ የርቀት ስራዎች (remote jobs) ተፈጥረዋል። እንዲህ አይነት አዳዲስ የሥራ ፈጠራ መስኮች እንዲስፋፉ ዜጎች በመንግስት የሚመቻቹ እንደ የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ አይነት የሥልጠና እድሎችን እና ሌሎች በግል ጥረት የሚገኙ የአቅም መገንቢያ መንገዶችን በመጠቀም ራሳቸውን ብቁ ማድረግ ይጠበቃል።

ይህን ለማሳካት በተለያየ ደረጃ ያሉ በርካታ የመንግስት ተቋማት ከፍተኛ ጥረትን የጠየቀ ቢሆንም ካለው ፍላጎት አንጻር ተጨማሪ ስራዎች እንደሚጠበቁ መንግስት ይገነዘባል። ለዚህም ፈጠራና ፍጥነት የታከለባቸው የፖሊሲና የተግባር ምላሾች ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ይጠበቃል። በዚህ አጋጣሚ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት፣ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሠራተኛ ማህበራት እና ሌሎችም ባለድርሻዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪውን ያስተላልፋል።

በድጋሜ እንኳን ለሠራተኞች ቀን በሰላም አደረሳችሁ!

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleያጋጠመው የጸጥታ ችግር በውይይት እና እርቅ ሊቋጭ እንደሚገባ የደብረ ማርቆስ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ተማሪዎች ተናገሩ።
Next articleለሀገሪቱ ልማት አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለው ሠራተኛ በኢኮኖሚውም በፍትሐዊነት መንገድ ተጠቃሚ ሊኾን ይገባል።