
ደብረ ማርቆስ: ሚያዝያ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ ተማሪዎች ጋር “የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክት በሠላም ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ የውይይት መድረክ ተካሄዷል። የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መልካሙ ሽባባው የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እና ሕዝቡን የሰላም ባለቤት ለማድረግ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
ከቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ ተማሪዎች ጋር የተደረገው ውይይት ጠቃሚ ግብዓቶች የተወሰዱበት እንደነበር ተናግረዋል። ጦርነት የችግር መፍቻ መንገድ ሊኾን ስለማይችል ውይይትን በማስቀደም የተከሰተውን የሰላም እጦት በንግግር መቋጨት እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰበት መኾኑንም ጠቅሰዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት የኢኮኖሚ ክላስተር አማካሪ አስናቀ ይርጉ ከተራዘመ ግጭት መውጣት እንደሚገባ ተናግረዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት ራስን ግጭት ውስጥ በማስገባት ሳይኾን በሰከነ መንገድ በመነጋገር መኾኑን ከተማሪዎች ጋር በተደረገው ውይይት በአጽንኦት መነሳቱን ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎች ሰላምን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ እና የራሳቸውን ጠቃሚ ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል ያለመ ውይይት ስለመደረጉም አብራርተዋል፡፡ አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የውይይቱ ተሳታፊ የኮሌጁ ተማሪዎች ግጭቱ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ከማስከተሉም በላይ እንደ ክልል በብዙ መንገድ ወደ ኋላ እንድንመለስ ያደረገ ክስተት መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው ያሉት የውይይቱ ተሳታፊ ተማሪዎች የነገ ህልማቸውን ለማሳካት እና ለሀገር አበርክቶ ለማድረግ ሰላም በእጅጉ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ጦርነት አውዳሚ በመኾኑ ከዚህ በላይ የከፋ ችግር ውስጥ እንዳንገባ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር በውይይት እና እርቅ ሊቋጭ ይገባል ብለዋል ተማሪዎች፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን