
ደብረ ብርሃን: ሚያዚያ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ከኾኑት ጉዳዮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚደረገው ጥረት ተጠቃሽ ነው። የተሻለ የደን ሽፋን ያላቸው ሀገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቅን የካርበን ልቀት በማመቅ ተጽዕኖውን የማስቀረት ፋይዳቸው ቀላል አይደለም።
የበለጸጉ ሀገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን በካይ ጋዝ ለመከላከል ለሚያደርጉት ጥረት ማበረታቻ ይኾን ዘንድም ገንዘብ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ዓለም አቀፍ ስምምነት ተደርሷል። ይህ ስምምነትም የካርበን ግብይት ይባላል። የካርበን ሽያጭ ደንን ከጭፍጨፋ በመከላከል እና ተጨማሪ በማልማት እንዲሁም የካርበን ልቀትን በመቀነስ ለሚከናወነው ሥራ የሚከፈል ዓለም አቀፍ ክፍያ ነው።
ክፍያው የሚፈጸመው ደግሞ የተሻለ የደን ሽፋን ላላቸው ሀገራት፣ ከባቢ ሥነ-ምሕዳርን የሚጠብቁ እና የአየር ንብረት ለውጥን ወጥነት ባለው መልኩ መከላከል ለሚችሉት ሀገራት ነው። በደን ልማት ዘርፍ እየተከናወነ ባለው ሥራ ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ 2030 ድረስ ከካርበን ሽያጭ 100 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል።
የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣንም የደን መመናመን ምጣኔን በመቀነስ እና የተጀማመሩ የደን ልማት ሥራዎችን በማሳለጥ ከዘርፉ ገቢ ለማግኘት እየተሠራ መኾኑን ጠቅሷል። የባለሥልጣኑ ምክትል ኀላፊ ተሾመ አግማስ ለአሚኮ እንዳሉትም የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራዎች ልዩ ትኩረት በማግኘታቸው የክልሉ የደን ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ይገኛል።
ዕድሉን በመጠቀም ወደ ካርበን ንግድ ሥርዓት ውስጥ ለመግባትም ግብዓት ከማሟላት ጀምሮ ጥረቶች መጀመራቸውን ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ ደን ልማት የሬድ ፕላስ ፕሮግራም አስተባባሪ ይተብቱ ሞገስ (ዶ.ር) በበኩላቸው እስካሁን የነበረው የሀገሪቱ የደን ሽፋን ሁኔታ ወደ ካርበን ሽያጭ ሥርዓቱ ለመግባት አያስችልም ነበር ነው ያሉት።
በመኾኑም የደን መመንጠርን ትርጉም ባለው መልኩ ማስቀረት፣ የካርበን ልቀትን በተሻለ መልኩ ማመቅ የሚችሉ ዝርያዎችን መርጦ በስፋት ማልማት ያስፈልጋል ብለዋል። እንደ ሀገር የሚመለከታቸውን አጋር እና ባለድርሻ አካላት በማስተባበር በስፋት እንደሚሠራበትም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን