
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ለተሻሻለው የከተማ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎቶች አዋጅ ቁጥር 291/2016 ማስፈጸሚያ በረቀቀው ደንብ እና በዘጠኝ ወሩ በተከናወኑ ሥራዎች ላይ በክልሉ ምዕራብ ቀጣና ከሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው ።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ይርጋ ዓለሙ ለባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ከሦስት ምንጮች እና ከ28 ጥልቅ ጉድጓዶች የንጹሕ መጠጥ ውኃ እየቀረበ ይገኛል ብለዋል። የከተማውን የውኃ አቅርቦት ሽፋን ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም ነው የገለጹት። በዚህ ዓመት በ200 ሚሊዮን ብር የአራት ጥልቅ ጉድጎዶች ቁፋሮ ሥራ ተሠርቷል፤ የመስመር ዝርጋታ ሥራም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የውኃ ጉድጓዶቹ ሲጠናቀቁ በሰከንድ 150 ሊትር ውኃ ማመንጨት የሚችሉ ናቸው። ጉድጓዶቹ ሙሉ በሙሉ ወደ አገልግሎት መሥጠት ሲጀምሩ የከተማው የውኃ ሽፋን ወደ 85 በመቶ እንደሚደርስ ነው የገለጹት። የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ጥላሁን ሽመልስ የንጹህ መጠጥ ውኃን ተደራሽ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት ሲሠራ ቆይቷል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተሠራው ሥራ ከ300 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። ባለፉት ዓመታት በተሠራው ሥራ የንጹህ መጠጥ ውኃን ሽፋን 76 በመቶ ማድረስ ቢቻልም በየጊዜው በሚነሱ ግጭቶች ምክንያት ከአገልግሎት ውጭ የኾኑ ተቋማት መኖራቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት የወጣው አዋጅ ቁጥር 188/2003 ዓ.ም አኹን ያለውን የሕዝብ ጥያቄ ሊሸከም የሚችል ኾኖ ባለመገኘቱ መሻሻሉንም ነው ምክትል ኀላፊው የገለጹት። በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 291/2016 የውኃ አገልግሎት ጽሕፈት ቤትን ወደ “ከተማ መጠጥ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት” እንዲቀየር ተደርጓል።
ከተቋም ስያሜ ባለፈ አዋጁ ከዚህ በፊት የነበሩ የመዋቅር፣ በተቋሙ እና በማኅበረሰቡ መካከል የነበሩ ተግባር፣ ኀላፊነት እና ግዴታዎችን፣ የቦርድ አደረጃጀት ችግሮችን የሚፈታ እንደኾነ ገልጸዋል።
ተቋሙም አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ የውስጥ የፋይናንስ አቅሙን በማጠናከር የተለያዩ ሥራዎችን እንዲሠራ እድል ፈጥሯል።
አኹን ላይ የማስፈጸሚያ ደንብ እየተዘጋጀ ሲኾን እንደጸደቀ ወደ ተግባር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን