ሰላምን ማስፈን ዓላማው ያደረገ ሕዝባዊ ውይይት በምዕራብ ጎጃም ዞን በተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ነው።

18

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጸጥታ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በዞኑ ውስጥ ባሉ በሁሉም የወረዳ እና የከተማ አሥተዳደር ቀበሌዎች ሕዝባዊ ውይይቶች እየተካሄዱ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን አስታውቋል። የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓባይ ዓለሙ የጸጥታ ችግሩ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥፋት ለማኅበረሰቡ ማስገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተሳሳተ መንገድ የተደናገረውን ሕዝብ ትክክለኛውን መንገድ ተከትሎ ለሰላም ዘብ እንዲቆም በየደረጃው ካለው ማኅበረሰብ ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ እንደኾነም ተናግረዋል። የሰላም ውይይቱ የተጀመረው አንጻራዊ ሰላም በሁሉም አካባቢዎች ተስፋፍቶ ኅብረተሰቡ ልማቱን እንዲቀጥል እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ነው ብለዋል።

ኅብረተሰቡ የሰላሙ ባለቤት ኾኖ እርስ በርስ በመመካከር እና ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በማድረግ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች እንዲቀጥሉ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ያደርጋል ነው ያሉት። ውይይቱ እስከ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም በየደረጃው ካለው ማኅበረሰብ ጋር ስለሚቀጥል በየደረጃው ማኅበረሰቡ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እና ትብብር ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዮናስ ሞላ የጸጥታ ችግሩ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ዓሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ እና የልማት ሥራዎች ላይ እንቅፋት እየፈጠረ ስለኾነ ወደ ጫካ የወጡ አካላት መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲመለሱ ኅብረተሰቡ መምከር አለበት ብለዋል።

የማኅበረሰብ አቀፍ ውይይቶች ፍሬያማ እንዲኾኑ በየደረጃው ያለው አካል ድጋፍ እና ትብብር ሊያደርግ ይገባል ብለዋል። አስተያየታቸውን የሰጡ የውይይቱ ተካፋዮች የጸጥታ ችግሩ የሰው ሕይዎት እየቀጠፈ፣ ንብረት እያወደመ እና የልማት ሥራዎችን እያደናቀፈ ስለኾነ መንግሥት ችግሮችን በሰከነ መንገድ እና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ምቹ ሁኔታዎችን ሊፈጥር ይገባል ብለዋል።

ወደ ጫካ የወጡ ወንድሞች ወደ ሰላማዊ መንገድ ተመልሰው ከማኅበረሰባቸው ጋር በሰላም እንዲኖሩ ለመምከር ዝግጁ መኾናቸውንም ከክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከጎንደር ቀጣና ባለድርሻ አካላት ጋር የሥራ አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው።
Next articleከ300 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ገለጸ።