
ጎንደር: ሚያዝያ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸምን ከጎንደር ቀጣና ባለድርሻ አካላት ጋር እየገመገመ ነው። በግምገማ መድረኩ ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከሌላው ጊዜ በባሰ የክልሉ የትምህርት ሥራ ችግር ላይ መኾኑ ተነስቷል።
የሠላም እጦቱ በትምህርት ሥራው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ቢያሳድርም ችግሩን ተቋቁሞ ሰፊ ተግባር እየተከናወነ መኾኑ ተነስቷል። የቢሮው ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ የነገን ሀገር ተረካቢ የኾኑ ተማሪዎችን ማስተማር ከራስ አልፎ ለሀገር የሚያበረክቱትን ትልም መሠነቅ መኾኑን አስረድተዋል።
በተፈጠረው የሰላም እጦት ወደ ትምህርት ገበታ ያልመጡ ተማሪዎች እንዲመለሱ ከሚደረገው ጥረት ባሻገርም በመማር ላይ ያሉ ተማሪዎችም ውጤታማ እንዲኾኑ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል። በትምህርት ገበታ ለሚገኙ ተማሪዎች የአዳር ጥናት፣ የቤተ መጽሐፍት አገልግሎት እና የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት የተሻለ ውጤት ያስመዘግቡ ዘንድም አበረታች ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለማሻሻል እየተሠራ ሲኾን ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ከ900 በላይ ብሎኮች እየተገነቡ እንደኾነ እና ከግማሽ በላይ የሚኾኑት ደግሞ መጠናቀቃቸውን ምክትል ቢሮ ኀላፊው ጠቅሰዋል። ማኅበረሰቡ የትምህርት ተቋማትን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት እያገዘ መኾኑን የገለጹት አቶ መኳንንት በበጀት ዓመቱ 2 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ 50 በመቶ መሳካቱንም ገልጸዋል።
ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ ባለው ጥረት የራሳቸውን ኀላፊነት እየተወጡ እንደኾነ የግምገማው ተሳታፊዎች ተናግረዋል። በትምህርት ዘመኑ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በልዩ ትኩረት እየተመራ እንደሚገኝ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ስንታየሁ ነጋሽ አንስተዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ክንዱ ዘውዱ በክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናዎች ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሥነ ልቦና ድጋፍ እና የማጠናከሪያ ትምህርቶች እየተሠጡ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አገኘሁ አበባው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን