
እንጅባራ: ሚያዝያ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች በወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂደዋል። በመድረኩ በግጭቱ ምክንያት የደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ “የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የኔዓለም ዋሴ በክልሉ ብሎም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተፈጠረው ቀውስ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን አስተጓጉሎ መቆየቱን ተናግረዋል። በክልሉ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው ቀውስ መቋጫውን እንዲያገኝ የመንግሥት ሠራተኞች ገንቢ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጠይቀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በተፈጠረው ግጭት የጠፋው የሰው ሕይዎት እና የወደመው ሀብት እና ንብረት የክልሉን ሕዝብ ወደ ኋላ የሚጎትት መኾኑን ተናግረዋል። በጦርነት የተጀመሩ ግጭቶች ሁሌም መቋጫቸው ሰላማዊ ውይይት ነው ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ ተጨማሪ ጥፋት ከመድረሱ በፊት ምክክርን ማስቀደም እንደሚገባም አንስተዋል።
ለመልካም አሥተዳደር እጦት መንስኤ የኾኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዲፈቱም ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን