“አማራ ኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96 ነጥብ 9 ሕዝብ በቀጥታ የሚነጋገርበት፤ የመፍትሄ ሃሳቦችንም የሚያፈልቅበት ጣቢያ ነው” ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ

20

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን” በሚል የአገልግሉት መመሪያው የሚታወቀው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን መረጃዎችን ወደ ሕዝብ ከሚያደርስባቸው ጣቢያዎች መካከል አማራ ኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96 ነጥብ 9 አንዱ ነው።

ጣቢያው ልክ በዛሬው ቀን ሚያዚያ 22/1994 ዓ.ም ከረፋዱ 4:00 ሰዓት ነበር ሥራ የጀመረው። ጣቢያው ሲጀመር ዘወትር ከ4:00 ሰዓት እስከ 6:00 ሰዓት ማለትም በቀን ለሁለት ሰዓታት ብቻ ነበር የሚደመጠው። አሁን ላይ ጣቢያው በ24 ሰዓታት ሥርጭት እና ሀገራትን በሚያካልል ሽፋን አገልግሎት እየሰጠ ነው። ዛሬ 23ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉንም እያከበረ ነው።

የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ እንዳሉት አማራ ኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96 ነጥብ 9 ይዘት እና ተደራሽነቱን በየጊዜው በማሳደግ ሕዝብን የሚያገለግል ጣቢያ ነው። በ23 ዓመታት ጉዞው ዕድሜውን ብቻ ሳይኾን ይዘት እና ተደራሽነቱንም እየጨመረ የተጓዘ ጣቢያ ስለመኾኑ ተናግረዋል።

ለሕዝብ መረጃ የሚሰጡ ብዙ ዝግጅቶች አሉት፤ ሲመሠረት ባሕር ዳር ከተማ ዙሪያ ታጥሮ የነበረውን የሥርጭት አድማሱንም ወደ ሁሉም የሀገሪቱ ክፍል እና ዲጂታል ሚዲያን በመጠቀም እስከ ውጭ ሀገራት ድረስ አስፍቷል ነው ያሉት።

አማራ ኤፍ ኤም 96 ነጥብ 9 በኢትዮጵያ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች የምሥረታ ታሪክ ሁለተኛው ስለመኾኑም ተናግረዋል። ጣቢያው በሙያ እና በሥነ ምግባር የላቁ ባለሙያዎችን ያፈራ እና የራሳቸው የኾነ ቀለም ያላቸው ፕሮግራሞችን ቀርጾ ለሕዝብ እያደረሰ የሚገኝ ስለመኾኑም አንስተዋል።

ጣቢያው ጠቃሚ ሃሳብ እና መረጃዎችን ነው ለሕዝብ የሚያደርሰው፤ የጣቢያው አድማጮች ባለቤቶች መኾናቸውን በመገንዘብ ጠቃሚ የሚሏቸውን ሃሳቦች ሁሉ በማምጣት ተሳታፊ መኾን አለባቸው ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

አሚኮ አማራ ኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96 ነጥብ 9 ተደራሽ በኾነባቸው ቦታዎች ሁሉ ቅድሚያ የሚከፈት፣ ቅድሚያ የሚወደድ እና ቅድሚያ የሚታመን እንዲኾን በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል። አሚኮ በአጠቃላይ ሰባት የሬዲዮ ጣቢያዎች እና ከ800 በላይ ባለሙያዎችን ይዞ የሚንቀሳቀስ አንጋፋ የሕዝብ የመረጃ ምንጭ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

አማራ ኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96 ነጥብ 9 ሕዝብን በብርታት እያገለገለ ነው፤ በተለይም ከወቅታዊ ሁኔታዎች አኳያ ሰላም ለሕዝባችን ምን ያሕል ፋይዳ እንዳለው በማመላከት ግንባር ቀደም ሚና ተጫውቷል ነው ያሉት። “ሕዝብ በቀጥታ የሚነጋገርበት፤ የመፍትሔ ሃሳቦችንም የሚያፈልቅበት ጣቢያ ነው” ብለዋል ዋና ሥራ አሥፈጻሚው።

የአሚኮ የዘገባ ዝግጅቶች ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ እና በሁሉም ዓይነት የቴክኖሎጂ አማራጮች በጥራት የሚቀርቡ እንዲኾኑ በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ ተናግረዋል።

አንጋፋው ጋዜጠኛ እና የአማራ ኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96 ነጥብ 9 ዳይሬክተር ብርሃኑ ክንዱ ጣቢያው በ23 ዓመታት ዕድሜው ብዙ ውጣ ውረዶችን ያለፈ ግዙፍ ጣቢያ ነው ብለዋል። ጣቢያው በየጊዜው የዘገባዎችን ቅርጽ እና ይዘት ለሕዝብ በሚመጥን መልኩ እያሻሻለ የሚጓዝ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

“አማራ ኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96 ነጥብ 9 የአድማጮች ጣቢያ ነው” ያሉት ጋዜጠኛ ብርሃኑ ክንዱ የጣቢያው ዝግጅቶች አብዛኛዎቹ በቀጥታ የሚተላለፉ እና ሕዝብ በቀጥታ በመስመር ላይ ገብቶ የሚሳተፍባቸው ናቸው ብለዋል።

ጣቢያው ተወዳዳሪ እንዲኾን የሚያስችሉ እና ላቅ ያለ ፋይዳ ያላቸው ፕሮግራሞች ተቀርጸው ወደ አድማጮች እየደረሱ ስለመኾኑም ተናግረዋል። የጣቢያው ባለሙያዎችም ሙያዊ ኀላፊነትን እና ሥነ ምግባርን ተላብሰው ሕዝብን ለማገልገል የሚተጉ ስለመኾናቸው ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ከአንጋፉ የጣቢያው ጋዜጠኞች መካከል ጋዜጠኛ ኃይሌ አበራ እና ጋዜጠኛ ዘላለም ጌታቸው እንዳሉት አማራ ኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96 ነጥብ 9 ሲጀመር በአንድ አካባቢ ተወስኖ የነበረውን ተደራሽነቱን አሁን ላይ በመላ የሀገሪቱ ክፍሎች ያሰፋ እና መላ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት ጣቢያ ኾኗል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article”የተስተጓጎለውን የትምህርት ዘርፍ ትኩረት ሰጥተን በመሥራት ማካካስ አለብን” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
Next articleግጭቶች ሁሌም መቋጫቸው ውይይት ነውና ተጨማሪ ጥፋት ከመድረሱ በፊት ምክክር ይቅደም።