
ደሴ: ሚያዝያ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከዞን እና ወረዳ መሪዎች፣ ርእሰ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች እና ባለድርሻ አካላት ጋር የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸም ግምገማ በደሴ ከተማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በክልሉ ያለው ግጭት በትምህርት ዘርፉ ላይ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል።
በበርካታ አካባቢዎች የመማር ማስተማሩ ሥራ ቢኖርም አኹንም በክልሉ ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንዳልኾነ ተናግረዋል። ይህም ትውልዱን ወደኋላ እንዲቀር እያደረገው ይገኛል ነው ያሉት።
ልጆቻችን ተወዳዳሪዎች እና ተመራማሪዎች እንዲኾኑ አሁን ብዙ መልፋት ይጠይቃል ያሉት ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉትን ተማሪዎች ውጤታማ እንዲኾኑ ማብቃት ይጠበቃል ብለዋል።
የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄን በማጠናከር ደግሞ በቀጣይ ዓመት ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ዝግጁ ማድረግ ይገባናል ሲሉ ጠቅሰዋል።
ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ ተማሪዎችን ለማምጣት እና ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመተባበር የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የተስተጓጎለውን የትምህርት ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ማካካስ እንደሚገባም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ተመስገን አሰፋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን