”ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ እና ፋይዳው፦

254

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ፋይዳ” ተብሎ የሚጠራው ዲጂታል መታወቂያ ለዜጎች መሰጠት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል ይደረግ የነበረው ምዝገባ እና የመታወቂያ መስጠት አኹን ላይ አገልግሎቱን በባንኮች እና በወኪል ግለሰቦች በኩልም ምዝገባ እየተካሄደ ነው፡፡

ለመኾኑ ፋይዳ ምን ጠቀሜታ ምንድ ነው? ዜጎችስ ጠቀሜታውን ምን ያህል ተረድተውታል? ስንል ለመታወቂያው ምዝገባ በሚከናወንበት እና የታተመው መታወቂያ በሚሰጥበት ቦታ ተገኝተን ጠይቀናል፤ ታዝበናል። ለመታወቂያው ሲመዘገቡ እና የተዘጋጀላቸውን መታወቂያ ሲቀበሉ ያገኘናቸው ተገልጋዮች እንዳሉት መታወቂያውን መውሰድ ይጠቅማል ሲባል ሰሙ እንጂ ስለ ጠቀሜታው የተሟላ እውቀት የላቸውም፡፡

አንዳንዶች ደግሞ በመኖሪያ ቤት ማኅበር ለመደራጀት እና ሌሎች ግልጋሎቶችን ለማግኘት ግዴታ በመኾኑ ነው አሉን። ሥራውን እየተገበረው በሚገኘው የኢትዮ ቴሌኮም ማኅበራዊ ገጽ ላይ እንደተገለጸው ግን ፋይዳ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ራዕይ በአጋርነት ለማሳካት እና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ራዕይ ለማፋጠን የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ፣ የመታወቂያ ሕትመትና ስርጭት፣ ማንነትን የማረጋገጥ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን በድረ ገጹ ተገልጿል።

ፋይዳ ምንድን ነው?

ፋይዳ የዲጂታል መታወቂያ ዓይነት ሲኾን የነዋሪዎችን የባዮሜትሪክ (የጣት አሻራ፣ የአይን አይሪስ እና የፊት ምስል) እንዲኹም የግል መረጃዎችን በመሰብሰብ አንድን ግለሰብ ልዩ በኾነ መልኩ እንዲታወቅ የሚያስችል ነው፡፡

የፋይዳ ጠቀሜታዎች
ለግለሰቦች:-
👉 ማንነታቸውን በሕጋዊ መንገድ በማረጋገጥ መሰረታዊ የዜግነት መብቶቻቸውን ለማግኘት ያስችላል፤
👉 የዜጎችን ፍላጎት ያገናዘበ አገልግሎት ያስገኛል፤
👉 ግላዊ መረጃዎችን በአግባቡ በመያዝ ለዝርፍያ እና ለሌሎች አደጋዎች እንዳይጋለጡ ያደርጋል፤
👉 ማንነትን ለማረጋገጥ ያስፈልግ የነበረውን የሰነዶች ማገላበጥ በማስቀረት ለፈጣን አገልግሎት ምቹ ነው፤
ለነጋዴዎች
👉 የተቋማትን የተንዛዛ አገልግሎት ቀልጣፋ ያደርጋል፤
👉 በንግድ ጥናቶች ትክክለኛውን የወደፊት አደጋ በመተንበይ የቅድመ መከላከል ሥራ ለመሥራት ያስችላል፤
👉 የተሳሳተ የማንነት መረጃ ይዘው ለሚቀርቡ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ለማጣራት ቀላል ስለሚኾን የተቋማት መጭበርበርን ይከላከላል፤
👉የማንነት ማረጋገጫዎች የመገልገያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መኾን እና አለመኾኑን ለማጣራት ሰነድ ማገላበጥ አይጠይቅም፤ የሰው ኀይል እና ጊዜን ይቆጥባል፤
ለዜጎች
👉 ዜጎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ማንነትን ለማረጋገጥ ቀላል ይኾናል፤
👉 በመረጃ እጥረት ምክንያት ያልተገባ የአገልግሎት አሰጣጥ አይኖርም፤
👉 በሀሰተኛ የማንነት መረጃ የትክክለኛ ዜጎችን አገልግሎት መውሰድን ያስቀራል፤
👉 የወረቀት አሠራር ሂደትን በማስቀረት የሰው ኀይል ብክነትን ያስቀራል፤
የሚመዘገበው ማን ነው
👉 ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ሕጋዊ ነዋሪ በሙሉ ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ብቁ ነው።
👉 በሕጋዊ መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ወይም የሌለው የተፈጥሮ ሰው እንዲኹም በሀገሪቱ ሕግ መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ወይም የሚሠራ የውጭ ሀገር ዜጋ ይካተታሉ፡፡
👉 ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በላይ የኾኑ ልጆች፤
👉 ኢትዮጵያዊ እና ኢትዮጵያዊ ያልኾኑ የነዋሪነት ማረጋገጫ ያላቸው፤
👉 የመኖሪያ አድራሻ ማረጋገጫ ሰነድ ያላቸውም ኾነ የሌላቸው፤
👉 ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪነታቸው “በአዋጁ መሰረት” የተሰጣቸው፤
👉 የት እንደሚኖሩ ምንም ዓይነት ሰነድ የሌላቸው ሰዎች የዲጂታል መታወቂያ ያለው ሰው እንደ ምስክር ይዘው በመቅረብ መመዝገብ ይችላሉ፤

ለምዝገባ አስፈላጊ ሰነዶች

የቀበሌ መታወቂያ፣ ፓስፖርት፣ የልደት የምስክር ወረቀት፣ የትምህርት ማስረጃ፣ የንግድ ምዝገባ ወይም የንግድ ፈቃድ የምስክር ወረቀት፣ የጋብቻ የምስክር ወረቀት፣ መንጃ ፈቃድ፣ የባንክ አካውንት ደብተር፣ የመኪና ሊብሬ፣ የቤት ካርታ፣ የሙያ ፈቃድ ማስረጃ፣ የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር/ መታወቂያ (ፎቶ ያለው)፣ የጤና መድኅን መታወቂያ፣ የጡረታ መታወቂያ፣ የሥራ ፈላጊ መታወቂያ፣ የተማሪነት መታወቂያ፣ የእድር እና የእቁብ ደብተር ዋናዎቹ ሲኾኑ በማንኛውም የመንግሥት አካል የሚሰጥ መታወቂያ እና የቀበሌ ሥራ አስኪያጅ የሚሰጠው ማረጋገጫም ተቀባይነት እንዳለው ተገልጿል።

በመላ ሀገሪቱ የኢትዮ ቴሌኮም የተመረጡ አገልግሎት መስጫ ማዕከሎች፣ አጋር ድርጅቶች እና ተንቀሳቃሽ የምዝገባ ጣቢያዎች አገልግሎቱን እንደሚሰጡ ነው ኢትዮቴሌኮም በድረ ገጹ ያስታወቀው። የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ በምዝገባ ወቅት በሰጡት ሞባይል ቁጥርዎ National ID በሚል ባለ 12 አሐዝ የፋይዳ ልዩ ቁጥር በጽሑፍ መልዕክት ይላካል።

ቁጥሩን ቴሌብር ሱፐርአፕ ላይ በመግባት 👉 “መተግበሪያዎች’’ የሚለውን በመጫን 👉 የብሔራዊ መታወቂያ ሚኒ አፕን በመምረጥ 👉 ቁጥሩን በማስገባት 👉 ለሕትመት ዝግጁ የኾነ (softcopy) መታወቂያዎን ማግኘት እንደሚቻልም ኢትዮቴሌኮም በድረ ገጹ አሳውቋል።

ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ የተመዝጋቢው ብቻ የኾነ 12 ዲጅት ያለው የፋይዳ መለያ ቁጥርን የያዘ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ለተመዝጋቢው ይደርሰዋል።

ከቴሌብር ሱፐርአፕ ጋር የተዋሐደ ”ብሔራዊ መታወቂያ” ሚኒ አፕሊኬሽን የፋይዳ መለያ ቁጥሩን በማስገባት የሕትመቱን ሶፍት ኮፒ ማግኘት ያስችላል፡፡

የፋይዳ መለያው በአጭር መልዕክት ካልደረሰ፣ ቁጥሩ ከጠፋ እና የፋይዳ ዲጂታል መለያውን በቴሌ ብር ሱፐር አፕ ማግኘት ያልቻለ ሰው https://id.et/help ብሎ በመጫን ወይም በ 9779 በመደወል መረጃ እና ድጋፍ ማግኘት እንደሚችል ተገልጿል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበአማራ ክልል የኮሌራ በሽታ መከላከል በምን ደረጃ ላይ ነው?
Next article”የተስተጓጎለውን የትምህርት ዘርፍ ትኩረት ሰጥተን በመሥራት ማካካስ አለብን” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)