በአማራ ክልል የኮሌራ በሽታ መከላከል በምን ደረጃ ላይ ነው?

24

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየተሠራ መኾኑን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) መዘገቡ ይታወሳል። የበሽታው አሁናዊ ሥርጭት እና የመከላከል ሥራ ምን እንደሚመስል በአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ማስተባባሪያ ማዕከል ቡድን መሪ አሞኘ በላይ በበሽታው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአማራ ክልል የኮሌራ በሽታ በተለያዩ ዓመታት እንደተከሰተ የጠቀሱት ቡድን መሪው ሐምሌ 8 ቀን 2015 ዓ.ም የተከሰተው እና ሚያዝያ 3 ቀን 2016 ዓ.ም የተከሰተውን አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅትም ከታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በተከሰተው በሽታ 2 ሺህ 115 ሕሙማን ሪፖርት መደረጉን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በክልሉ በ5 ወረዳዎች በሽታው መኖሩን ተናግረዋል። በምዕራብ ጎንደር ዞን በቋራ ወረዳ፣ በሰሜን ጎጃም ዞን ባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ፣ በባሕር ዳር ከተማ፣ በአዊ ብሔረሰብ ዞን በጃዊ ወረዳ እና በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ከተማ መኾናቸውንም ዘርዝረዋል። በሽታው በፍጥነት የሚተላለፍ መኾኑን የገለጹት ቡድን መሪው በደንብ ከተሠራ እና ሁሉም አካል የሚጠበቅበትን ከተወጣ ግን በአጭር ጊዜ መቆጣጠርም እንደሚቻል ተናግረዋል።

በሽታውን ለመቆጣጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል። ክስተቱ ባለባቸው ቦታዎች ላይ ጊዜያዊ የሕክምና ጣቢያዎች ተቋቁመዋል። የታመሙትም ተለይተው ሕክምና እየተሰጣቸው መኾኑን ነው የተናገሩት። ለበሽታው የተጋለጡ አካባቢዎች ተለይተው የማከም እና ብክለትን ለመከላከል እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

ከክልል እስከ ጤና ተቋም ድረስ በሽታውን በመከላከል እና መቆጣጠር ሥራ ላይ በውይይት እየተሠራ መኾኑን የገለጹት ቡድን መሪው በክልል ደረጃ በየሳምንቱ ግምገማ እየተደረገ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉም አንስተዋል። ነገር ግን አሁንም በሽታውን ተቋጣጥረነዋል ማለት ስለማያስችል ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል።

የኮሌራ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሁሉም አካል የሚጠበቅበትን መሥራት እንደሚጠበቅበትም አንስተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪ ኤክስፖው ባለሀብቶችን ወደ አካባቢው የምንስብበት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article”ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ እና ፋይዳው፦