“ሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪ ኤክስፖው ባለሀብቶችን ወደ አካባቢው የምንስብበት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

34

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪ ኤክስፖ በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ በሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪ ኤክስፖው ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሀሴን (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የኮምቦልቻ ከተማ እና አካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ጸጋ ያለው አካባቢ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከተማዋ ተቻችሎ የመኖር ተምሳሌት መኾኗን አስገንዝበዋል፡፡ ኮምቦልቻ እና አካባቢው የሀገር በቀል ዕውቀት ባለቤት የኾነ አካባቢ መኾኑን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ ሌሎችም ከዚሁ አካባቢ ሊማሩበት እና ሊወስዱት የሚገባ ጉዳይ መኖሩን ነው የጠቆሙት፡፡

የማኅበረሰቡ መስተጋብር ለሌሎች ትምህርት የሚሰጥ እንደኾነም ተናግረዋል። ኮምቦልቻ ከተማ በታሪክ ከ1950 አጋማሽ አካባቢ ጀምሮ ከሌሎች ከተሞች በተለየ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ልቃ እየወጣች የነበረች ከተማ እንደኾነችም አንስተዋል። ከዚያ በኋላ ያለው ሁኔታ ለከተማዋ ዕድገት የማይመች እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

በእንስሳት እና ጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ምርት የታደለች ከተማ መኾኗን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ ለገቢ እና ወጭ ንግድ ምቹ መኾኗንም ገልጸዋል። ከተማዋ ለወደብ ቅርብ መኾኗ ለልማት ምቹ እና ተመራጭ እንድትኾን እንዳስቻላትም አመላክተዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ ሰላም ፈላጊነት ለልማት ተመራጭ እንድትኾን እንዳስቻላት ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ይህም ባለሀብቶች ከተማዋን መርጠው ለኢንቨስትመንት እንዲመጡ እንዳስቻላት ነው ያስገነዘቡት፡፡

ከባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ በክልሉ የሰላም መደፍረስ ሲከሰት ኮምቦልቻ እና አካባቢው በሀገር ሽማግሌዎች እና በሃይማኖት አባቶች አማካኝነት በአካባው ችግር እንዳይኖር ማድረግ እንደቻሉ አውስተዋል፡፡ በዚህ ዓመትም በግብርና እና በማዕድን ሀብት ባለሀብቶች ከተማዋን መርጠው እየመጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ከተማዋ እና ማኅበረሰቡ የሰላም አምባሳደር በመኾናቸው የመጣ ነው ብለዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሆቴል ቱሪዝም ለመሰማራት የሚፈልጉት እየተበራከቱ እንደሚገኙም ነው ያብራሩት፡፡ “ሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪ ኤክስፖው በምሥራቅ አማራ ያለውን የመልማት ጸጋ ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝም ያላቸውን ዕምነት” ገልጸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ባለሀብቶችን ወደ አካባቢው የምንስብበት ነው ብለዋል።

መድረኩ የምርት ሰንሰለትን የሚያጠናክር ሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪ ኤክስፖ እንደሚኾን ነው የገለጹት። የአካባቢው ማኅረሰብም ሰላሙን በማስጠበቅ እና ልማቱን እንዲያጠናክርም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ጀግና ሕዝብ ማለት ምን እና ማን እንደሚጠቅመው የሚያውቅ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleበአማራ ክልል የኮሌራ በሽታ መከላከል በምን ደረጃ ላይ ነው?