
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪ ኤክስፖ በኮምቦልቻ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡ በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሀሴን (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የገበታ ለትውልድ አንዱ አካል የኾነውን የሐይቅ ሪዞርትን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ትልቅ ጸጋ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ እዚህ እንዲደርስ ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
የሐይቅ ሪዞርት ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ታምርት የሚለው መሪ መልዕክት የኢትዮጵያን ማንሰራራት ከሚያበስሩት መሪ መልዕክቶች አንዱ ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ጸጋ እና ባለ ብዙ እሴት ሀገር ናት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለብዙ ጸጋ እና ባለ ብዙ እሴት ለኾነ ሀገር ደግሞ ዋና መገለጫው አምራችነት ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ይሄን መታወቂያዋን ትታ ሌላ መታወቂያ አውጥታ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
መታወቂያዋ ድህነት እና ኋላ ቀርነት፣ ጦርነት እና ግጭት ኾኖ እንደ ነበር የሁላችንም የቅርብ ትዝታ ነው ብለዋል፡፡ አሁን ለመሻገር ጫፍ ላይ እንዳለን ሁላችንም እናውቃለን ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ ታምርት የሚለው ተነሳሽነት ይህንን የተሳሳተ መታወቂያ በአዲስ መታወቂያ የመቀየር ስትራቴጂ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ታምርት ሁለት መሠረተ ሃሳቦችን የያዘ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ በኩል ከውጭ ሀገር የሚመጣውን ግብዓት እና ሸቀጥ በሀገር ውስጥ መተካት ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያ ብዝኀ ምርት እንዲኖራት እና የኢትዮጵያ ምርቶች የዓለም ገበያዎችን እንዲያጥለቀልቁ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
አምራችነት ሰላምን አጥብቆ ይፈልጋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምራችነት እና ሰላም የተንሰላሰሉ መኾናቸውን ደሴ እና ኮምቦልቻ ምስክሮች መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ “ጀግና ሕዝብ ማለት ምን እና ማን እንደሚጠቅመው የሚያውቅ ነው” ብለዋል፡፡ የደሴ እና የኮምቦልቻ ሕዝብ ማን እንደሚጠቅመው አውቋል ነው ያሉት፡፡
የማይጠቅሙትን አርቋል፣ ተከላክሏል፣ የሚጠቅሙትን ደግሞ አቅርቧል፣ ለልማት እና ብልጽግና ጊዜውን፣ ዕውቀቱን እና ጉልበቱን ሰውቷል ብለዋል፡፡ ማን እና ምን እንደሚጠቅመው የሚያውቅ ሕዝብ የሚያገኘውን ትርፍ በዓይኑ ማየት የሚፈልግ ካለ ኮምቦልቻ ይምጣ ይጎብኝ ነው ያሉት፡፡
ግጭት ጠማቂዎች ዓላማ ቢሶች ናቸው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነርሱ ደብዳቤ መላላኪያ ፖስታዎች ማለት ናቸው ብለዋል፡፡ የራሳቸው መልዕክት፣ የራሳቸው ዓላማ፣ የራሳቸው ፍላጎት እንደሌላቸውም ገልጸዋል፡፡ ሌላ ሰው የሰጣቸውን መልዕክት ግን ይዘው ይዞራሉ፣ ይንከራተታሉ ነው ያሉት፡፡
ግብርና ያማቸዋል፣ ኢንዱስትሪ ያስጠላቸዋል፣ ዕድገት ያቅራቸዋል፣ ዘመናዊነት ራሳቸውን ያዞራቸዋል፣ ትምህርት እና ሥልጣኔ ሆዳቸውን ይቆርጣቸዋል፣ አይመቻቸውም ነው ያሉት፡፡ ካላጠፉ አይደሰቱም፣ ካልገደሉ አይረኩም፣ ካላበላሹ የሠሩ አይመስላቸውም፣ ስለታቸው ሁሉ ሕዝብ ሲደኸይ አሳየን የሚል ይመስላል ብለዋል፡፡ አኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ከማንኛውም የሀገር እና የሕዝብ ጠላት ጋር እንደሚያብሩ እና እንደሚወዳጁም ገልጸዋል፡፡
የደሴ እና ኮምቦልቻ ሕዝብ ኢትዮጵያ ታምርት ሲሉት፣ የሰላም ጠላትንም እንመክት ይላል ነው ያሉት፡፡ የደሴ እና ኮምቦልቻ ሕዝብ ፎርጅድ ገንዘብ ትክክለኛ መስሎ የማያታልለው ብልህ ሕዝብ መኾኑንም ተናግረዋል። የአካባቢ ሰላም እንዴት እንደሚጠበቅ ከደሴ እና ኮምቦልቻ መማር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ጊዜው በዘመናዊ መሳሪያ ለሚያመርቱ እንጂ ኋላ ቀር ጠመንጃ ለሚያነግቱ አይደለም፣ አይመችምም ነው ያሉት፡፡ ጊዜው በኢንዱስትሪ መንደሮች ገብተው ለሚሠሩ እጆች እንጂ በየጉራንጉሩ በሰባራ ክላሽ ለሚተኩሱ፣ ለሚዞሩ አይደለም፣ አይመችም፣ ጊዜው የይቅርታ እና የመደመር እንጂ፣ የቂም በቀል እና የመቀናነስም አይደለም ነው ያሉት፡፡
ጊዜው በሀገራዊ የጋራ አጀንዳ ላይ በመመካከር ልዩነትን በውይይት የመፍታት እንጂ ወንድም ወንድሙን በጠላትነት የማየት፣ ሀገርን ከጠላት ጋር ለማድማት አብሮ የማሴርም አይደለም ብለዋል፡፡
መንግሥት ለሰላም እና ለይቅርታ በሩ ክፍት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ለክልሉ እና ለሀገር ዕድገት ደንቃራ የኾኑ ኃይሎች በይቅርታ ተመልሰው ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ መንግሥት በሰላማዊ መንገድ እንደሚቀበላቸውም አስታውቀዋል፡፡
በሰላም ለገቡ ኃይሎች እና ለክልሉ ሰላም እየሠሩ ላሉትም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ የሰላም ጥሪውን ባልተቀበሉ ኃይሎች ላይ ግን የምናደርገውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት፡፡
በጊዜያችን እንወቅበት፣ በዘመናችን እናምርትበት፣ ጊዜው የማረሻ እንጂ የመተኮሻ አይደለምና፣ ጊዜው የማምረቻ እንጂ የመሻኮቻ አይደለምና፣ ጊዜው የጫካ ፕሮጀክት እንጂ የጫካ ተኩስ አይደለምና፣ ጊዜው አምርቶ የመለወጥ እንጂ የሰው ሃብት የመቀማት አይደለምና ብለዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
