“ወሎ ከሁሉም በላይ ሰውነት ይቀድማል የሚል ማኅበረሰብ የሚኖርበት ነው” አቶ መሐመድአሚን የሱፍ

21

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪ ኤክስፖ በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሀሴን (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ የወሎ ኮምቦልቻ ትልቁ ጸጋ አብሮነት ነው ብለዋል፡፡ “ከሁሉም በላይ ሰውነት ይቀድማል የሚል ማኅበረሰብ የሚኖርበት አካባቢ መኾኑንም” ተናግረዋል፡፡

አብሮነት እና መከባበር ለዘመናት የተገነባ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ ወሎ ኢትዮጵያውያን በመስተጋብር የሚኖሩበት ነው ብለዋል፡፡ ከየትኛው አቅጣጫ ለሚነሳ ጽንፈኛ አስተሳሰብ ቦታ እንደሌላውም ገልጸዋል፡፡

አካባቢው ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረገ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ታላላቅ ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች፣ ታላላቅ የሃይማኖት አባቶች የሚገኙበት ነውም ብለዋል፡፡

በጥበቡ ዘርፍም አራቱ ቅኝቶች የሚገኙበት፣ ታላላቅ ሰዎች የፈለቁበት፣ እንግዳ መቀበል ባሕል የኾነበት አካባቢ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡

ኮምቦልቻ የኢንቨስትመንት እና የሎጂስቲክስ ማዕከል መኾነኗም አንስተዋል፡፡ ኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ማዕከል ኾና በታሪክ እንድትጻፍ እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው ባለሀብቶች በትውልድ አካባቢያቸው ማልማት እንደሚጠበቅባቸውም አንስተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ኤክስፖው የተዘጋጀው የአካባቢውን ጸጋ ለማወቅ እና ለመጠቀም ነው ብለዋል፡፡ ከተማ አሥተዳድሩ የወደፊት እጣ ፈንታውን የሚወስኑ የልማት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

ከተሞች የሚያድጉት መንግሥት፣ ባለሀብቶች እና ነዋሪዎች በአንድነት ሲሠሩ ነው ብለዋል፡፡ የአዋሽ ኮምቦልቻ- ሐራ ገብያ የባቡር መስመር አገልግሎት እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየታጠቁ ኃይሎች ለሰላም ዝግጁ እንዲኾኑ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡
Next article“ጀግና ሕዝብ ማለት ምን እና ማን እንደሚጠቅመው የሚያውቅ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ