የታጠቁ ኃይሎች ለሰላም ዝግጁ እንዲኾኑ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

26

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በሁሉም ቀበሌዎች ውስጥ የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በአማራ ክልል ተከስቶ የቆየው የሰላም እጦት የክልሉን ሕዝብ ለበርካታ ጉዳቶች እየዳረገው ይገኛል፡፡ ግጭቱ ባስከተለው ቀውስም ማኅበረሰቡ ያለ ስጋት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የዕለት ከዕለት ተግባራትን ማከናወን ባለመቻሉ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

ግጭቱ በክልሉ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን የገለጹት ነዋሪዎቹ ትምህርት እና ሌሎች ልማቶች በመስተጓጎላቸው በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች ወደ ኋላ እንዲቀሩ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። ከተራዘመ ጦርነት ያተረፍነው ውድመት እና ሰብዓዊ ቀውስ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ ጦርነቱ ያስከተለውን ጉዳት በመገንዘብ ሰላም ሰፍኖ በየአካባቢው የተቋረጡ የልማት እንቅቃሴዎች በተረጋጋ መንገድ ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ያጋጠመው ግጭት በውይይት እልባት አግኝቶ ማኅበረሰቡ እየደረሰበት ካለው ስቃይ እና እንግልት እንዲወጣ የታጠቁ ኃይሎች ለሰላም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል፡፡ በደብረ ማርቆስ ከተማ የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ በሚል መሪ መልዕክት በ19 ቀበሌዎች እና ከ60 በላይ በሚኾኑ ሰፈሮች ነው ውይይት የተካሄደው፡፡

የውይይቱ አሥተባባሪ እና የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ አበባዉ ግዛቸው አጋጥሞ ከቆየው ውስብስብ ችግር ለመውጣት መንግሥት ለውይይት እና ለምክክር ቅድሚያ ሰጦ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የጸጥታ ችግሩ በጋራ እልባት አግኝቶ ሀገራዊ አንድነትን ለማምጣት በጋራ መሥራት የሁሉም ኀላፊነት ነዉ ብለዋል፡፡

ግጭት እንዲቆም እና ሰላም እንዲመጣ ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጎን ኾኖ እየሠራ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ማኅበረሰቡ ለሰላም እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ በቀጣይ ከገባንበት የግጭት አዙሪት እና ዳግም ጉዳት በዘላቂነት በመውጣት ስለ ሰላም እና ልማት የሚያስብ ማኅበረሰብ መፈጠር አለበት ነው ያሉት፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበሙያቸው አስተዋጽኦ ለማድረግ ሰላም እንደሚያስፈልግ የባንጃ ወረዳ መምህራን ተናገሩ።
Next article“ወሎ ከሁሉም በላይ ሰውነት ይቀድማል የሚል ማኅበረሰብ የሚኖርበት ነው” አቶ መሐመድአሚን የሱፍ