
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የቀበሌ ነዋሪዎች ”የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል ርእስ የተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልምን በመመልከት ለሰላም ዘብ ለመቆም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ በውይይቱ የተሳተፉት አቶ ሲሳይ ከበደ እንዳሉት ”የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” ፊልም የጥፋትን አስከፊነት እና የሰላምን አስፈላጊነት ተገንዝቤበታለሁ ብለዋል፡፡
በፊልሙ መነሻነት የአካባቢዬን ሰላም ከራሴ ውጭ ማንም ሊጠብቅልኝ እንደማይችል ትምህርት ወስጄበታለሁ ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ወገኖች ለሰላም እጃቸውን ሊዘረጉ ይገባልም ብለዋል፡፡ ሌላው ተወያይ አቶ መኳንንት ሽቴ በበኩላቸው “የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” ፊልም በርካታ ትምህርት ቤቶች እና በርካታ መሰረተ ልማቶች መቋረጣቸውን አይቻለሁ ብለዋል፡፡ የሕዝብ ፍልሰትንም ተመልክቸበታለሁ ነው ያሉት፡፡ በመኾኑም ማኅበረሰቡ ሰላምን ይሻል፤ ለሰላም ዝግጁነንም ብለዋል፡፡
ወይዘሮ ትዕግስት አወቀ እንዳሉት ”የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” ፊልም ከሰው ልጅ የማይጠበቅ ዘግናኝ ድርጊቶችን ተፈጽመው በማየቴ ከልቤ አዝኛለሁ ነው ያለሁት፡፡ ስለኾነም ጦርነት ለማንም አይበጅምና ሁሉም ሰላምን ለማስፈን መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡ በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን ላለፉት ሁለት ዓመታት አካባቢ ክልሉን ለማፍረስ የጽንፈኝነት አደጋ ተጋርጦ ነበር ብለዋል፡፡
የተፈጠረውን ችግር ከመጀመሪያው ጀምሮ የክልሉ መንግሥት እና የከተማው አሥተዳደር ከሕዝቡ ጋር መወያየቱን አስታውሰዋል፡፡ ጽንፈኝነት በየአካባቢው ያደረሰውን አደጋ እና ጉዳት ብሎም ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎችን ሕዝቡ በመወያየት በእጅጉ አውግዞታል ነው ያሉት፡፡
ሕዝቡ የጽንፈኝነትን አደጋ ተረድቷል ያሉት አቶ ሞላ በሂደት ችግሩን ከመንግሥት ጋር ኾኖ ለማስተካከል ሰፊ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷልም ብለዋል፡፡ አኹንም ቢኾን ሰላምን ለማጽናት ሕዝብን አቅም አድርጎ መሥራት አስፈልጓል ብልዋል፡፡ በርካታ ለውጦችም ተገኝተዋል ነው ያሉት፡፡
በጽንፈኛው ኀይል የሚፈጸሙ ጥፋቶችን ሕዝቡ በዓይኑ እያየ ችግሩን ለማስቆም ከመንግሥት ጎን በቁርጠኛነት እየሠራ ነውም ብለዋል፡፡ የተጎዱ የልማት አውታሮች መልሰው እንዲጠገኑለት ሕዝቡ እየጠየቀ መኾኑን ኀላፊው አስታውሰዋል፡፡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱለት እየጠየቀ ነውም ብለዋል፡፡ ሕዝቡ ሰላሙን ለማስጠበቅ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ለውጡን ቀጣይ ለማድረግ ከሕዝቡ ጋር በዛሬው ዕለት በ27 ቀበሌዎች፣ በ92 ቀጣናዎች ”የጥፋት እጆችና መዘዞቹ ” በሚል ርእስ የተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም ለሕዝብ ለእይታ ቀረቧል ብለዋል ፡፡ ከ38 ሺህ በላይ ሕዝብም ተሳትፎበታል ነው ያሉት፡፡
በዘጋቢ ፊልሙ መነሻነት ሕዝቡ የጽንፈኛውን ድርጊት እየተቃወመ ሰላም መሻቱን አሳይቶበታል ብለዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
